የብልፅግና ፓርቲ  (ብልፅግና)  መተዳደሪያ ደንብ (ረቂቅ)  


የብልፅግና ፓርቲ (ብልፅግና)  መተዳደሪያ ደንብ 

መግቢያ  


በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) እና በአጋር ድርጅቶች አመራር በአገራችን ያስመዘገብናቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦችን አስጠብቆ ለማስፋት፣ ስህተቶችን ለማረም እና የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የድርጅታችንን ቅርጽና ይዘት ወቅቱ ለሚጠይቀው ትግል በሚመጥን መልኩ መቀየር በማስፈለጉ፤ 
የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች ሀገር በመራንባቸው ዓመታት በአመዛኙ ተመሳሳይ የፖለቲካ ዓላማ፣ ፕሮግራም እና መሰረታዊ አቅጣጫ እየገነባን የመጣን በመሆኑ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል እና ስህተቶችን በማረም ወደ ሚቀጥለው የትግል ምዕራፍ ለመሸጋገር አስቻይ አቅም ያለን በመሆኑ፤ የምናካሂደው ውህደት እያንዳንዱ ድርጅት የነበረውን የአላማና የተግባር ውህደት በአዲስ መንፈስ ይበልጥ በማጠናከር የተሻለ ኃይል እንድናሰባስብ የሚያስችለን በመሆኑ፤ 
  • በኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔዎች የፓርቲ ውህደት አጀንዳ በተከታታይ ቢነሳም ሳይወሰንና ሳይፈፀም መቆየቱን ግምት ውስጥ በማስገባት 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የዝግጅት ስራዎች በፍጥነት ተጠናቀው ድርጅቶቹ ወደ ውህደት እንዲሸጋገሩ ያስቀመጠውን አቅጣጫ መፈፀም በማስፈለጉ፤ 
  • ሀገራችን ኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እና የተለያዩ ማንነቶች በጋራ ባካበቱት እሴት የተገነባችና የጋራ ራዕይ ያላቸው ህዝቦች መኖሪያ ህብረ ብሄራዊት ሀገር መሆኗን በመገንዘብ፣ 

  • የሃገራችን ኢትዮጵያን እድገትና የጋራ ብልፅግና እውን ለማድረግ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ፣ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኢኮኖሚ ስርዓት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት፣ 
  • ቀጣይነት ያለው ብልፅግናን የሚያረጋግጥ ሁለንተናዊ ማህበራዊ ልማትና ሀገራዊ ክብርን ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት፣ 
  • አገራችንን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለማሻገር አዲስ ራእይና አዲስ ትርክት እንደሚያስፈልግ በማመን፣ 
  • የሕግ የበላይነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት፤ የግለሰብና ቡድን መብቶች በሚዛኑ የሚከበሩባት፤  የበለፀገች፣ ሕብረ-ብሔራዊ ማንነቷ የዳበረና አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ባለን ቁርጠኝነት፣ 
  • ይህንንም ለመተግበር በመደመር አስተሳሰብና በአንድነት ቅኝት በመነሳት፣ ልናያት የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመገንባት የእያንዳንዳችንን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት የበኩላችንን ሚና ለመጫወት በከፍተኛ ቆራጥነት ተሰባስበን መታገል በማስፈለጉ፣ 

የብልፅግና ፓርቲ (ብልፅግና) የሚመራበት የመተዳደሪያ ደንብ መቅረጽ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ 
ይህ መተዳደሪያ ደንብ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የተደነገጉትን ህጎች የሚያከብር የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ (ብልፅግና) ሰነድን በመስራች ጉባዔያችን መክረንበት ህጋዊ የፓርቲው ሰነድ አድርገን አጽድቀናል። 

ምዕራፍ አንድ ጠቅላላ ድንጋጌዎች 

አንቀጽ 1. ርዕስ ይህ መተዳደሪያ ደንብ “በብልፅግና ፓርቲ መሥራች ጉባኤ የጸደቀ የብልፅግና ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል። 
አንቀጽ 2. የፓርቲው መጠሪያ የፓርቲው መጠሪያ  “የብልፅግና ፓርቲ” በእንግሊዘኛ Prosperity Party ነው። 
አንቀጽ 3. የፓርቲው አርማ ………አርማ……. 
አንቀጽ 4. የአርማው ትርጉም አርማው  የሀገራችንን ህብረ ብሄራዊነትን፣ ሀገራዊ አንድነትንና ብሄራዊ ኩራትን፤ ሰላምን፤ ዴሞክራሲንና የብልፅግና አስተሳሰብ የያዘ ሆኖ ከውስጥ ወደ ውጭ እየሰፋ የሚሄድ የቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ትስስሮችን የሚያመላክት ይሆናል። 

አንቀፅ 5. የፓርቲው የስራ ቋንቋ/ዎች 
ሀ. ፓርቲው ለሁሉም የአገራችን ቋንቋዎች ሙሉ እውቅና ይሰጣል፤ 
ለ. የፓርቲው የስራ ቋንቋ ክልሎች በህገ መንግስታቸው የስራ ቋንቋ ይሆናሉ ብለው ያጸደቋቸው ቋንቋዎች ይሆናሉ። 
ሐ. ክልሎችና የአካባቢ ቅርንጫፍ ፓርቲ ፅ/ቤቶች የየራሳቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ቢያንስ አንድ የፓርቲውን የስራ ቋንቋ በተጨማሪነት መጠቀም አለባቸው። 

አንቀጽ 6. የፓርቲው ልሳን 1) የፓርቲው ልሳን “ብልፅግና” ነው። 2) የፓርቲው ልሳን በፓርቲ የስራ ቋንቋዎች የሚዘጋጅ ብዝሃ ልሳን ነው። 3) የዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (2) እንደተጠበቀ ሆኖ በሌሎች ተጨማሪ ሀገራዊና የውጭ ቋንቋዎች ሊዘጋጅ ይችላል።
  
አንቀጽ 7. የፓርቲው  ዋና ጽህፈት ቤት እና ቅርንጫፍ  ፅ/ቤቶች 1) የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ ይሆናል፤ 
2) የፓርቲው ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች በየክልሎች ዋና ከተማዎች እና ለፌዴራል መንግስት ተጠሪ በሆኑ ከተማ አስተዳደሮች ይሆናሉ፤  
3) የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ (2) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ፓርቲው በዞን፤ በወረዳና በቀበሌ እንዲሁም እንደአስፈላጊነት ኢትዮጵያውን በብዛት ባሉባቸው ውጭ አገራት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሊያቋቁም ይችላል። 

አንቀፅ 8. የፓርቲው የአደረጃጀትና አሰራር መርሆዎች 1) ዓላማ የብልፅግና ፓርቲ አላማ ጠንካራ፣ ዴሞክራሲያዊና ቅቡልነት ያለው ዘላቂ ሀገረመንግስት  እና ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያሰፍን ማህበራዊ ልማት ማረጋገጥ እና ሀገራዊ ክብርን ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት ማካሄድ ነው። 
2) የፓርቲው መርሆዎች፤ ሀ) ህዝባዊነት፤ ለ) ዴሞክራሲያዊነት፤ ሐ) የህግ የበላይነት፤ መ) ተግባራዊ እውነታ፤ ሠ) ሀገራዊ አንድነትና ህብረ-ብሄራዊነት፤  

3) ፓርቲው እሴቶች፤ 

ሀ) የህዝቦች ክብር፣ 
ለ) ፍትህ 
ሐ) ህብረ-ብሄራዊ አንድነት፤

 4) የፓርቲው የአሰራር መርሆዎች፤ 

1) ፓርቲው የአገሪቱን ሕገ መንግስት እና ሌሎች የፌደራሉና የክልሎች ሕጎችን በማክበር ተግባራቱን ያከናውናል፤ 
2) አባላት በፓርቲ መድረክም ሆነ ከመድረክ ውጭ የግል ሃሳባቸውን የማንጸባረቅ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በፓርቲው የተወሰነውን የማስፈጸም ሃላፊነት አለባቸው፤
3) በፓርቲው የውሳኔ ሒደቶች አንድ አባል አንድ ድምጽ ብቻ ይኖረዋል፤ 
4) የፓርቲ ውሳኔ በየደረጃው ዴሞክራሲያዊ ውይይት ከተካሄደበት እና የጋራ ግንዛቤ ከተያዘበት በኋላ በተባበረ ድምፅ እንዲወሰን ጥረት ይደረጋል። 
5) በተባበረ ድምፅ ለመፅደቅ ባልቻሉ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚተላፈው በአብላጫ ድምፅ ይሆናል። ተፈፃሚነቱም በወሰነው አካል እና በታችኛው መዋቅር ይሆናል፤ 
6) በሌላ አኳኋን የተደነገገ ከሌለ በስተቀር የፓርቲው ውሳኔ የሚያልፈው ከሃምሳ በመቶ በላይ ድምጽ ካገኘ ነው። ድምጽ በሁለት እኩል የተከፈለ ከሆነ ሰብሳቢው ያለበት ወገን ድምጽ አሸናፊ ይሆናል።  
7)  በዚህ ደንብ በተለየ አኳሃን ካልተደነገገ በስተቀር የትኛውም የፓርቲው መዋቅር ምልዓተ-ጉባኤ ተሟልቷል የሚባለው ከጠቅላላው የጉባኤው ወይም ከስብሰባው ተሳታፊዎች ውስጥ 50%+1 እና ከዚያ በላይ ሲገኙ ነው፤ 
8) በሁሉም ስብሰባዎች በተለይም የአስቸኳይ ስብሰባዎች ሁሉም የሚመለከታቸው አባላት የመገኘት ግዴታ አለባቸው። ሆነ ብሎ ምልዐተ ጉባኤ እንዳይሟላ ማድረግ የተከለከለ ነው፤ ምልዐተ ጉባኤ እንዳይሟላ ያደረገ በዲሲፒሊን ይጠየቃል፤ 
9) በየትኛውም ደረጃ በተወሰነ ውሳኔ ላይ ከተሰብሳቢ አባላት 1/3ኛ  የሚሆኑት እንደገና እንዲታይ ጥያቄ ካቀረቡ ጥያቄው ለውይይት ክፍት ሆኖ እንደገና ውሳኔ ይሰጥበታል፤ 
10) በአንድ መድረክ ላይ በተወሰነ ውሳኔ ላይ አቤቱታ ቀርቦ በዚያው መድረክ ተቀባይነት ካገኘ ድጋሚ አቤቱታ አይቀርብም። በጉዳዩ ላይ አቤቱታ ማቅረብ የሚቻለው በተግባር እየፈፀሙ በሂደት በሚከፈት የጉባኤ/ኮንፈረንስ አጋጣሚ ወይም የፅሁፍ ፊርማ በማሰባሰብ ብቻ ይሆናል። 
11) እንደገና ይታይልን የሚል ጥያቄ የወሰነው አካል በጉባኤ ላይ ባለበት በቃል ወይም በፅሁፍ አቤቱታው ሲቀርብ ጉዳዩ ከላይ በቀረበው መሰረት ይታያል። ወሳኙ አካል ከተበተነ ደግሞ በፅሁፍ አቤቱታ በመጠየቅ ሊቀርብ ይችላል።  
12) አቤቱታ አቅራቢው አቤቱታውን በፅሁፍ አዘጋጅቶ ለሰብሳቢው ያቀርባል። ሰብሳቢው አቤቱታው ወደሚመለከታቸው አባላት ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማሰራጨት አቤቱታውን የሚደግፉ ሁሉ እንዲፈርሙ ያደርጋል። ከሚመለከታቸው አባላት ውስጥ 1/3ኛው ከፈረሙ ጉዳዩ በሚቀጥለው መደበኛ ወይም አስቸኳይ ስብሰባ ላይ እንዲታይ ይደረጋል። 
13)  ሁሉም የፓርቲው አሰራሮች በግልጽነትና ዲሞክራሲያዊነት ላይ የተመሰረቱ ይሆናሉ፣ 
14)  በፓርቲው ከፍተኛ የአመራር አካላት የሚወሰኑና በሀገሪቱና በህዝቦቿ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ አቋሞችና ውሳኔዎች ሁሉ ውሳኔውን ባስተላለፈው አካል በሚስጥር ተጠብቆ እንዲቆይ ካልተወሰነ በስተቀር ከአስፈላጊው ማብራሪያ ጋር ለአባላትና እንዳስፈላጊነቱ ለህዝብ ይገለፃሉ። 
15) በልዩ ሁኔታ በሚስጥርነት ተጠብቀው ሊቆዩ የሚችሉ ጉዳዮች በህዝቦች ሰላምና አንድነት፣ በሀገር ደህንነት እና በፓርቲ ህልውና ላይ ጉዳት የማስከተል ውጤት ያላቸው ብቻ ናቸው። 
  
16) በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲ አመራር አካላት ለወሰኗቸው ውሳኔዎች በሙሉ ሃላፊነት ይወስዳሉ። በተጨማሪም ሃላፊነትን ያለመወጣት ወይም ከተሰጠ ሃላፊነት ውጪ መሰማራት ተጠያቂነት ያስከትላል። 
17) ተጠያቂነትም እንደሁኔታው በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ወይም በሀገሪቱ ህጎች መሰረት ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ ወይም ህጋዊ እርምጃዎችን ያስወስዳል። 
18)  በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አካላት የስራ እንቅስቃሴያቸውን የሚያሳይ ዝርዝር እቅድና ሪፖርት በወቅቱ የማቅረብ ሃላፊነት አለባቸው፤ የበላይ አካላትም ወቅታዊ ግብረ መልስ መስጠት አለባቸው። 
19)  አባላትና አደረጃጀቶች የስራ አፈፃፀም ውጤታማነታቸውን የሚመዝኑባቸውና እርስ በርስ የሚማማሩባቸው መደበኛ የውይይት ጊዜያት ይኖራቸዋል። 
20)  ፓርቲው በሁሉም ደረጃዎች የወጣቶችና የሴቶች ክንፎችን የማሳተፍና የማብቃት አቅጣጫና አሰራርን ይከተላል። 
21)  ፓርቲው ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነቶች በማዕከላዊነት የሚወሰኑ ይሆናል። 
22) ልዩ ድጋፍ የሚሹና አናሳ ቁጥር ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የፓርቲው አባላትና አደረጃጀቶች በየደረጃው ተገቢውን ውክልና እንዲያገኙ ይደረጋል። 
23) የፓርቲው አላማዎች፣ ፕሮግራምና እቅድ ተግባራዊ የሚሆኑት በፓርቲው ዋና ፅ/ቤት፣ በክልልና በየደረጃ ባሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች፣ በፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በልማት ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎች እና በውጪ ሀገር በሚኖሩ የፓርቲው መዋቅሮች  አማካኝነት ይሆናል። 

ምዕራፍ ሁለት አባልነት 

አንቀጽ 9. የፓርቲው አባል ስለመሆን ከዚህ በታች የተመለከቱትን መመዘኛዎች የሚያሟላ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የፓርቲው አባል መሆን ይችላል። 
ሀ) የፓርቲውን ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ተቀብሎ በጽናት ተግባራዊ ለማድረግ ፍቃደኛ የሆነ፣ 
ለ) መልካም ስነ ምግባር ያለውና በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያለው፣ 
ሐ) በህብረ ብሄራዊነት እና በሀገራዊ አንድነት ላይ ፅኑ አቋም ያለውና ዋልታ ረገጥ አመለካከትና ተግባሮችን በፅናት የሚታገል፣ 
መ) ዜጎችንና ህዝቦችን በእኩልነት የሚያገለግል፣ የህዝብ ጥቅምን የሚያስቀድም፣ ከሙስናና ብልሹ አሰራሮች ራሱን ያራቀና ሌሎችንም የሚታገል፣   
ሠ) የፓርቲውን ዕሴቶችና ዓላማዎችን ተቀብሎ የተሰጠውን ሃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ የሆነ፤ 
ረ) በፓርቲው መመሪያ መሠረት ወርሃዊ የገንዘብ መዋጮ ለመክፈል ፈቃደኛ የሆነ፤ 
ሰ) ዕድሜው አስራ ስምንት ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆነ፣ 
ሸ) የሌላ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ፣ 
ቀ) የፖለቲካ ድርጅት አባል የመሆን መብቱ በሕግ ያልተገፈፈ፤ 
በ) በዚህ ደንብ በተወሰነው መሠረት የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ የፓርቲው አባል መሆን ይችላል። 

አንቀጽ 10. ለአባልነት የሚቀርብ ጥያቄ 
1)  አንድ የፓርቲው አባል ለመሆን የወሰነ ዜጋ በአካባቢው ለሚገኘው የፓርቲው ጽህፈት ቤት በጽሁፍ ማመልከት ይኖርበታል፤ 
2) ከላይ በንዑስ አንቀፅ (1) የተቀመጠው እንደተጠበቀ ሆኖ በየደረጃው የሚገኝ የፓርቲው መዋቅር ለፓርቲው ፕሮግራምና መተደደሪያ ደንብ ታማኝና ለተግባራዊነቱም ይታገላል ብሎ ያመነበትን ግለሰብ ለፓርቲው አባልነት ሊመለምለው ይችላል፤ 
3)  በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1) እና (2) መሰረት መሥፈርቱን አሟልቶ የተመለመለ ግለሰብ ለስድስት ወራት በሙከራ አባልነት ይቆያል፤ 
4)  የፓርቲው ጽ/ቤት የእጩ አባሉን አፈጻጸም አይቶ ሙሉ አባል የማድረግ ወይም ተጨማሪ ከሶስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ የእጩነት ጊዜውን ማራዘም ይችላል፣  
5) የእጩ አባልነት ቆይታ ከአንድ ጊዜ በላይ አይራዘምም፣ 
6) እጩ አባሉ በሙከራ ጊዜ ቆይታው ፓርቲው የሚሰጠውን ተልዕኮ ይፈጽማል፣  
7)  የአባላት ምልመላ፣ ግንባታ፣ ስምሪት፣ ምደባ፣ ምዘናና ስንብት ዝርዝር መመሪያ በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ይወጣል።  

አንቀጽ 11. የአባል መብት  
1) ማንኛውም የፓርቲ ሙሉ አባል የሚከተሉት መብቶች ይኖሩታል፣  
ሀ) በፓርቲው አካላት ምርጫዎች የመምረጥና የመመረጥ፣ 
ለ) በፓርቲው ጉባኤዎች የመሳተፍ፣ በውይይት የመካፈልና በድምጽ በሚወሰኑ ጉዳዮች ላይ ድምጽ የመስጠት፣ በማንኛውም ጉዳይ ላይ በህጋዊ መድረኮች ሃሳቡን በጽሁፍም ሆነ በቃል የማቅረብ፣ 
ሐ) በማንኛውም የፓርቲ አካል ወይም አባል ላይ በመረጃ የተደገፈ ሂስ የማቅረብ፣ 
መ) በየትኛውም የፓርቲ ውሳኔ ቅር ከተሰኘ ቅሬታውን በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት በየደረጃው ለሚመለከተው አካል የማቅረብ፤ 
ሠ) ስለራሱ፣ ስለአካሉ፣ ስለፓርቲው ማወቅ የሚገባውን ነገር እስከ ፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የመጠየቅና መልስ የማግኘት፣ 
ረ) የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ፣ ፕሮግራም፣ አቋሞችና ውሳኔዎች ለሌሎች የማሳወቅ፣ የማስተዋወቅ፣ የማስረፅና በተጨባጭ እንዲተገበር የማድረግ እና 
ሰ) በየትኛውም ጊዜ በጽሁፍ አመልክቶ እና በእጆቹ የሚገኙ የፓርቲው ንብረቶች እና ሃላፊነት በአግባቡ አስረክቦ መልቀቅ ይችላል።

2) ማንኛውም ዕጩ አባል በየደረጃው ለፓርቲው አካላት የመምረጥና የመመረጥ እንዲሁም ድምጽ የመስጠት መብት የለውም፤ የሌሎች የአባልነት መብቶች ግን ተጠቃሚ ሲሆን፣ የግዴታዎችም ተገዥ ይሆናል። 

አንቀጽ 12. የአባል ግዴታ ማንኛውም የፓርቲ አባል የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩበታል፤ 
1) በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ የፓርቲውን ፕሮግራም፣ መመሥረቻ ጽሁፍ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ መመሪያዎች፣ ውሳኔዎችና ዕቅዶችን የማወቅ፣ የመቀበል፣ የማክበር፣ የመገዛት እና ለተግባራዊነታቸው በግንባር ቀደምትነት የመታገል፣ 
2) በሚገኝበት የሥራ መስክና የኃፊነት ደረጃ የፓርቲውን አንድነት፣ ጥራትና ጥንካሬ፣ የፓርቲውን የፖለቲካ እሳቤዎች ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ሙሉ ተሳትፎ የማድረግ፣ 
3) የፓርቲውን መርሆዎች፣ ዕሴቶችና የአባላት የሥነ ምግባር ሕጎችን ማክበር እና የፓርቲውን፣ የህዝብና የሀገርን ደህንነትና ሉዓላዊነት የመጠበቅ፣ 
4) የአገሪቱን ሕጎችና ልዩ ልዩ መንግስታዊ ውሳኔዎች ማክበር፣  
5) በሀገራዊና አካባቢያዊ ምርጫ ወቅት የምርጫ ካርድ የማውጣት፣ 
6) የፓርቲውን አንድነት፣ ጥራትና ጥንካሬ የሚጎዱ ማናቸውንም ዝንባሌና ድርጊቶችን የማጋለጥና የመታገል፣ 
7)  በፓርቲው ውስጥ በግለሰቦች ወይም ቡድኖች የተያዙ ተናጠል አቋሞችን የፓርቲው በማስመሰል በማናቸውም መልኩ በሚዲያ ከማሰራጨት የመቆጠብ፣ 
8)  በአባላት መካከል የሚኖረውን መልካም ግንኙነት ከሚያጎድፉ ድርጊቶች የመታቀብ፣ 
9)  በፓርቲው ውሳኔ መሠረት የአባልነት መዋጮ የመክፈል፤ 
10)  የፓርቲው ንብረት በአግባቡ የመጠቀም፣ 
11)  ከሙስና የፀዳ፣ ሙስናንና አድሏዊ አሰራርን የመታገልና የማጋለጥ ግዴታ እና 
12)  ከአንድ አካባቢ ወይም የስራ ቦታ ወደሌላ አካባቢ ወይም የስራ ቦታ በቋሚነት ለቅቆ ሲሄድ የለቀቀበትን እና የደረሰበትን የፓርቲ መዋቅር ማሳወቅ አለበት። 

አንቀጽ 13. በአባላት ላይ በዲስፒሊን ጉድለት ስለሚወሰዱ እርምጃዎች 
1) ማንኛውም አባል በሚከተሉት ሁኔታዎች ከቃል ማስጠንቀቂያ ጀምሮ ከአባልነት እስከ ማሰናበት የሚደርስ ርምጃ ሊወሰድበት ይችላል፤  
ሀ) የፓርቲውን ፕሮግራም፣ ደንብ፣ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ያላከበረ ወይም ሌሎች ጥፋቶችን የፈጸመ አባል ወይም ዕጩ አባል ጉዳዩ በዝርዝር ታይቶ ማስረጃ ከተገኘበት እንደጥፋቱ ክብደት የዲስፒሊን እርምጃ ይወሰድበታል፣ 
ለ) በፓርቲው አባላትና ዕጩ አባላት በሚፈፀሙ ጥፋቶች ላይ የሚወሰደው የዲስፒሊን እርምጃ የፓርቲውን ሥነ ምግባር ለማዳበር፣ ስህተቶችንና ጉድለቶችን ለማረምና የፓርቲውን ጥራትና ጥንካሬ ለመጠበቅ የሚያገለግል መሆን አለበት፣ 
ሐ) ማንኛውም አባል የፓርቲውን የአባልነት መዋጮ በተከታታይ ለ6 ወራት አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ካልከፈለ እና ውዝፍ መዋጮውን ለመክፈል ፍቃደኛ ካልሆነ ከአባልነቱ በራሱ ፈቃድ እንደለቀቀ ይቆጠራል፣ 
መ. ማንኛውም አባል በትክክለኛ መረጃ ላይ ሳይመሰረት አባላትን መመልመል ወይም ከአባልነት ማግለል፣ 
ሠ. ማንኛውም አባል የሌላ ፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆኑ ከተደረሰበት፣ የብልፅግና ፓርቲ አስተሳሰቦችን ለመናድ በተጨባጭ ሲንቀሳቀስ የተገኘ እንደሆነ ከፓርቲ አባልነቱ ይሰረዛል፣ 
ረ) የፓርቲው አባላትና ዕጩ አባላት የሚፈጽሟቸው ጥፋቶች ክብደት እየታየ የሚከተሉት እርምጃዎች ይወሰዳሉ፤ 
1. ለሙሉ አባል 
 ሀ) ተግሳጽ፣ 
 ለ) የቃል ወይም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ 
 ሐ) ከኃላፊነት ማገድ፣ 
 መ) ከአባልነት መሠረዝ፣ 
2. ለዕጩ አባል 
ሀ) የዕጩ አባልነት የሙከራ ጊዜ ማራዘም፣ 
ለ) ከዕጩ አባልነት መሰረዝ፤ 
ሸ) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ (1) ፊደል (ረ) እርምጃ የተወሰደበት አባል ወይም ዕጩ አባል አቤቱታውን በየደረጃው ላለው የፓርቲው የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ያቀርባል፣  

2) የአባላት የዲስፒሊን ጉድለት እርምጃ አወሳሰድ ማዕከላዊ ኮሚቴው በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ይፈጸማል፤ 

ምእራፍ ሶስት የፓርቲው አወቃቀርና አደረጃጀት 

አንቀጽ 14. የፓርቲ አወቃቀርና የአመራር አካላት 
1) የፓርቲው ድርጅታዊ አወቃቀር የአገሪቱን ህገ መንግስታዊ ፌዴራላዊ አወቃቀር የተከተለ ነው፣ 
2) ፓርቲው የሚከተሉት ቋሚ አካላት ይኖሩታል። 
ሀ) ብሔራዊ ጉባዔ፣ 
ለ) ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ 
ሐ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ 
መ) ፕሬዝዳንት 
ሠ) ምክትል ፕሬዝዳንት 
ረ) ማዕከላዊ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን፣ 
ሰ) የፓርቲው ጽህፈት ቤት  
ሸ) የፓርቲው የክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች 
ቀ) የፓርቲው የአካባቢ አካላት  
በ) የሴቶች አደረጃጀት 
ተ) የወጣቶች አደረጃጀት  

3) የፓርቲው መሰረታዊ ድርጅቶች በአባላት የሥራና የመኖሪያ ቦታ የሚደራጁ ሲሆን፣ በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በዞንና በክልል ደረጃ ይቋቋማሉ። 

አንቀፅ 15. የብሄራዊ ጉባዔ፣ የክልል ጉባዔና የኮንፈረንሶች አወቃቀር  
ሀ) የፓርቲው ብሔራዊ ጉባዔ፣ የክልል ጉባዔዎችና እና ከዞን እስከ ቀበሌ ያሉ ኮንፈረንሶች በዋነኛነት የህዝብ ቁጥርንና የአባላት ብዛት መሰረት ያደረገ ሆኖ አናሳ ቁጥር ያላቸውን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አባላት ውክልና ባረጋገጠ መልኩ ይዋቀራሉ፣ 
ለ) በብሔራዊ ጉባዔ፣ በክልል ጉባዔና ከዞን እስከ ቀበሌ ባሉ ኮንፈረንሶች በየደረጃው የፓርቲውን እንቅስቃሴ የሚመሩ አመራር አካላት ይመረጣሉ። 
ሐ) ብሔራዊ ጉባዔ ማዕከላዊ ኮሚቴውን ይመርጣል፣ የክልል ጉባዔ የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴን፣ የዞንና የወረዳ እና የቀበሌ ኮንፈረንስ የየአደረጃጀታቸውን አመራር ኮሚቴዎች ይመርጣሉ። 
መ) የፓርቲው ብሔራዊ ጉባዔ ማዕከላዊ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽንን፣ የክልል ጉባዔ የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲውን የኦዲት ኮሚሽን፣ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ የፓርቲው ኮንፈረንሶች የየአደረጃጀታቸውን ኦዲት ኮሚሽን ይመርጣሉ። 
ሠ) የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት በፌዴራል አካላት፣ በውጪ ሀገራት፣ በመንግስት የልማት ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎች የሚሰሩ የፖለቲካና ድርጅት ስራዎችን የሚያስተባብሩ ኮሜቴዎችን ያደራጃል። አደረጃጀቶቹ ከዞን እስከ ቀበሌ ኮንፈረንስና የአመራር አካላት ይኖራቸዋል። ዝርዝር አፈፃፀሙን የሚመለከት መመሪያ  በማዕከላዊ ኮሚቴ ይወጣል።  

አንቀጽ 16- የፓርቲው ብሄራዊ ጉባኤ 
1) የፓርቲው ብሔራዊ ጉባኤ የፓርቲው ከፍተኛ የአመራር አካል ነው፤ 
2) የፓርቲው መደበኛ ብሔራዊ ጉባኤ በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ ይካሄዳል፤ 
3) የፓርቲው አስቸኳይ ጉባኤ በሁለት ዓመት ተኩል የሚካሄድ ሆኖ፣ ቀድሞ በተካሄደው መደበኛ ጉባኤ የተካፈሉት ጉባዔተኞች በቀጥታ ይሳተፋሉ።  
4) የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በድምፅ ብልጫ ሲወስን አስቸኳይ ጉባዔ ሊጠራ ይችላል። 
5) የፓርቲው ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የቋሚ ጉባኤ አባላትን 1/3ኛ የድጋፍ ድምፅ ካገኘ አስቸኳይ ጉባዔ እንዲጠራ ሊያደርግ ይችላል። የአስቸኳይ ጉባኤ ምልዓተ ጉባዔ 50%+1 ነው። 
6) ለፓርቲው ጉባኤ የሚያስፈልጉ የዝግጅት ሥራዎች በሥራ አስፈጻሚ እና በፓርቲው ዋና ፅ/ቤት በሚቋቋም የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ይከናወናሉ፤ 
7) የማዕከላዊ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላት በቀጥታ በጉባኤው ይሳተፋሉ፤ 
8) በአንቀፅ 14 ንዑስ አንቀፅ 1 (ሀ) የተቀመጠው እንደተጠበቀ ሆኖ የጉባኤው የውክልና ሥርዓት ማዕከላዊ ኮሚቴው በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ይፈፀማል፤ 
9) ከፓርቲው አባላት መካከል ቢያንስ 2/3ኛው በጉባኤው ላይ ሲገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል።  
10)  ለመደበኛ ጉባዔ ቢያንስ ከሁለት ወር በፊት ጥሪ መተላለፍና አጀንዳዎቹም መገለጽ አለባቸው፣ አስቸኳይ ጉባዔ ከአንድ ወር በፊት የጥሪ ጊዜና አጀንዳዎቹ መገለጽ አለባቸው፣  
11)  ብሔራዊ ጉባኤው የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል:-  
ሀ) የፓርቲውን ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ ያጸድቃል፣ ያሻሽላል፤ 
ለ) ፓርቲው የሚመራባቸውን አቅጣጫዎችንና እቅዶችን ይነድፋል፣ 
ሐ) የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የማዕከላዊ የቁጥጥርና ኢንሰፔክሽን ኮሚሽን አባላት ቁጥር ይወስናል፣ ይመርጣል፤ 
መ) የማእከላዊ ኮሚቴ፣ የማዕከላዊ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽንና እንደአስፈላጊነቱ በሌሎች አካላት የሚቀርቡለትን ሪፖርቶችን ያዳምጣል፣ ይገመግማል፣ ያፀድቃል፤ 
ሠ) ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገውን የውህደት ወይም የቅንጅት ወይም በፕሬዚዳነቱ የተደረገ ስምምነት የውሳኔ ሀሳብ ያጸድቃል፤ 
ረ) የማዕከላዊ ኮሚቴ እና የማዕከላዊ የቁጥጥርና ኢንሰፔክሽን ኮሚሽን አባላት ዕገዳና ስንብት ላይ ውሳኔ ይሰጣል፤  
ሰ) የፓርቲውን ስምና ዓርማ ያጸድቃል፣ያሻሽላል፣ ይለውጣል። 
ሸ) ጉባኤው መደበኛው ሥራውን ከመጀመሩ በፊት በዝግጅት ኮሚቴ የሚቀርብለትን የጉባኤ ዝግጅት ሪፖርትና የሥነ ሥርዓት ደንብ መርምሮ ያጸድቃል፤   

አንቀጽ 17. የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ  1) የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ጉባኤው ሆኖ በጉባዔዎቹ መሀል ፓርቲውን የሚመራ ከፍተኛ አካል ነው።  2) ማዕከላዊ ኮሚቴው በቀጥታ በነጻና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከጉባዔው አባላት በሚስጢር ድምፅ አሰጣጥ በሚመረጡ አባላት የሚመሰረት ነው፤ 3) የማዕከላዊ ኮሚቴው አባላት ብዛትና ስብጥር በጉባዔው ይወሰናል፤ ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ በማዕከላዊ ኮሚቴ ይወጣል፤ 4) ማእከላዊ ኮሚቴው በየስድስት ወሩ መደበኛ ጉባኤ ያደርጋል፤ ሆኖም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካመነበት ወይም ከማዕከላዊ ኮሚቴው አባላት መካከል አንድ ሦስተኛ ሲጠይቁ ከዚህ ባነሰ ጊዜ አስቸኳይ ጉባኤ ሊጠራ ይችላል፤ 
  
5) የማዕከላዊ ኮሚቴ ምልዓተ-ጉባዔ ከአባላቱ ከ50% +1 የተገኙበት ይሆናል፤ 6) በማዕከላዊ ኮሚቴ የተላለፈ ማንኛውም ውሳኔ በሁሉም የፓርቲው መዋቅሮችና አካላት ተፈፃሚ ይሆናል፤ 7) የማዕከላዊ ኮሚቴ  በፓርቲው ፕሬዚዳንት እና/ወይም ምክትል ፕሬዚዳንት ይመራል፤  8) የማዕከላዊ ኮሚቴው ተጠሪነት ለብሔራዊ ጉባኤው ነው። 9) ማዕከላዊ ኮሚቴው የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል:-  
ሀ) የፓርቲውን ፕሮግራምና ደንብ፣ የጉባዔው ውሳኔዎች ሥራ ላይ መዋላቸውን ያረጋግጣል፣ 
ለ) በፓርቲው ጉባኤ በሚቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ፓርቲውን በበላይነት ይመራል፤ የፓርቲውን አጠቃላይ አቅጣጫዎችና እቅዶችን እንዲሁም ማስፈጸሚያ  መመሪያዎችን ያመነጫል፣ አፈጻጸማቸውን በየጊዜው ይገመግማል፤ 
ሐ) የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴን ሪፖርት ያዳምጣል፣ ይገመግማል፣ ውሳኔ በሚሹ ነጥቦች ላይ ይወስናል፤ 
መ) የምርጫ ስትራቴጂ ያጸድቃል፣ ለምርጫ የሚደረገውን ሂደት በበላይነት ይመራል፤ 
ሠ) አስፈላጊ የሆኑ ድርጅታዊ መዋቅሮችን ይዘረጋል፣  
ረ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ቁጥር ይወስናል፣ 
ሰ) የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ አመራር ኮሚቴን ይመራል፣ 
ሸ) የፓርቲውን ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ይመርጣል፣ 
ቀ) የፓርቲውን ልሳን ዋና አዘጋጅ ይመድባል፤ 
በ) የማዕከላዊ ኮሚቴውን ዓመታዊ የሥራ ዕቅድና የፓርቲውን በጀት ያጸድቃል፤  
ተ) በፓርቲው መተዳዳሪያ ደንብ ትርጓሜ ላይ ለሚነሱ ክርክሮች ውሳኔ ይሰጣል፣ 
ቸ) ደንቡን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ዝርዝር መመሪያዎችን ያጸድቃል፣ 
ነ) ለፓርቲው ፕሮግራምና ደንብ ተገዢ ያልሆኑና የአመራር ብቃት የጎዳላቸውን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በ2/3ኛ ድምጽ ያግዳል፤ 
  
ኘ) የፓርቲውን ግቦችና የዚህን መመሥረቻ ጽሁፍ ድንጋጌዎች ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ተግባራትን ሁሉ ያከናውናል፤ 
አ) የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴዎችን ይሰይማል፣ 

አንቀጽ 18. የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ  
1) የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለማዕከላዊ ኮሚቴ ሆኖ፤ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል በሚስጥር ድምጽ ይመረጣል፣ 
2) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቁጥር በማዕከላዊ ኮሚቴ ይወሰናል፣ 
3) የስራ አስፈጻሚው ጉባኤ በፓርቲው ፕሬዝዳንት ይመራል። 
4) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መደበኛ ስብሰባውን በሶስት ወር አንድ ጊዜ ያደርጋል፣ 
5) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ በፕሬዝዳንቱ ወይም ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት 1/3ኛ ከጠየቀ ከዚህ ባነሰ ጊዜ ሊጠራ ይችላል፤ 
6) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምልዓተ ጉባዔ ከአባላቱ ከ50% +1 የተገኙበት ይሆናል፤ 
7) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል:- 
 ሀ) በጉባዔውና በማዕከላዊ ኮሚቴ የሚወጡ ዕቅዶች፣ ውሳኔዎችና መመሪያዎች መከበራቸውንና በሥራ ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፣ አመራር ይሰጣል፣ 
ለ) የጉባዔውንና የማዕከላዊ ኮሚቴውን ውሳኔዎች መሠረት በማድረግ የህብረተሰቡን ኑሮ እንዲሻሻልና አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር አስፈላጊውን ስልት ይቀይሳል፣ መመሪያ ይሰጣል፣ ተግባራዊ መሆናቸውን ይከታተላል፣ 
ሐ) ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን የሚያጠናክሩና የፌዴራል ስርዓቱን የሚያጎለብቱ የፖሊሲ ሃሳቦችን ያመነጫል፤ መተግበራቸውን ይከታተላል፤ 
መ) የጉባዔውና የማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔዎችን መሠረት በማድረግ የፓርቲውን ውስጣዊ ድርጅታዊ ሕይወት የበለጠ ለማዳበር የሚያስችሉ መመሪያዎች ያወጣል፣ ተግባራዊ መሆናቸውን ይከታተላል፣ ሠ) ለማዕከላዊ ኮሚቴው የሥራ ዕቅድና ሪፖርት ያቀርባል፣ 
ረ) ለፓርቲው ጽ/ቤት የዕለት ተዕለት ሥራ መመሪያ ይሰጣል፤ 
ሰ) የፓርቲውን ዋና ፅ/ቤት ሃላፊና ምክትል ሃላፊ ይመድባል፣ 
ሸ) የፓርቲውን ልሣን ቦርድ አባላት ይሰይማል፣ 
ቀ) የማዕከላዊ ኮሚቴ አጀንዳ ያዘጋጃል፣ 
በ) የፓርቲው ፕሮግራም፣ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ለፓርቲው አባላት እና ለመላው ሕዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ ስልት ይቀይሳል፣ ተግባራዊ መሆኑን ያረጋግጣል፣ 

አንቀጽ 19. የፓርቲው ፕሬዝዳንት 1) የፓርቲው ፕሬዝዳንት ተጠሪነቱ ለማዕከላዊ ኮሚቴ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል:-  
ሀ) የማዕከላዊ ኮሚቴና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጉባኤዎችን በፕሬዝዳንትነት ይመራል፣ 
ለ) የማዕከላዊ ኮሚቴና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስራዎችን ያስተባብራል፣ 
ሐ) የማዕከላዊ ኮሚቴና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔዎችን ያስፈጽማል፣ 
መ) ፓርቲውን በመወከል ከተለያዩ አካላት ጋር የስራ ግንኙነት ያደርጋል፣ ስምምነቶችን ይፈርማል፤ 
ሠ) የሥራ ሪፖርቱን ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያቀርባል፤  
ረ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጉባኤዎች አጀንዳ ያዘጋጃል፤ 
ሰ) በማዕከላዊ ኮሚቴ እና በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል። 

አንቀጽ 20. የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት 
1) የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ተጠሪነቱ ለፕሬዝዳንቱ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል:-  
ሀ) ፕሬዝዳንቱ በማይኖርበት ጊዜ ፓርቲውን ይመራል፤ 
ለ) በፕሬዝዳንቱ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባሮች ያከናውናል። 

አንቀጽ 21. ማዕከላዊ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን   
1) ማዕከላዊ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ከብሔራዊ ጉባኤ በሚመረጡ አባላት ይዋቀራል፤ የኮሚሽኑ አባላት ብዛት በጉባዔው ይወሰናል፤ 
2) ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለፓርቲው ብሔራዊ ጉባኤ ነው፤ 
3) ኮሚሽኑ ቋሚ ጽህፈት ቤትና ሠራተኞች ይኖሩታል፤ 
4) ኮሚሽኑ በየደረጃው የራሱን የበታች መዋቅሮች በፓርቲው ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ያደራጃል፤ 
5) ኮሚሽኑ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡-  
  
ሀ) ኮሚሽኑ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብና የአሠራር መመሪያዎች በሥራ ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፣ 
ለ) የጉባዔ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በአግባቡ መፈፀማቸውን ይከታተላል፣ 
ሐ) የፓርቲው አባላትና ዕጩ አባላት የፓርቲውን ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብና መመሪያ ማክበራቸውን፣ ለጠበቀ ዲስፕሊን ተገዢ መሆናቸውን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፣ 
መ) የፓርቲው ሥራዎች ከፓርቲው መሠረታዊ መርሆችና መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም ሌሎች መመሪያዎች አኳያ መፈጸማቸውን ይከታተላል፤ 
ሠ) የፓርቲውን ጥራትና ጥንካሬ ለማዳበር አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል፣ 
ረ) የፓርቲው አባላት መብቶች እና ጥቅሞች መከበራቸውን ይከታተላል፤ 
ሰ) ከአባላት የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ይቀበላል፣ ይመረምራል፣ የእርምት የውሳኔ ሀሳቡን ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያቀርባል፤ 
ሸ) በኮሚሽኑ የሚቀርበውን የእርምት ሃሳብ ሥራ አስፈጻሚው ካልተቀበለው ለማዕከላዊ ኮሚቴው ይቀርባል፤ ማእከላዊ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ እስከ ጉባኤ ድረስ ተፈጻሚ ይሆናል፤ 
ቀ) የፓርቲው ገንዘብ፣ ንብረትና ሰነዶች በአግባቡ መጠበቃቸውን ቁጥጥር ያደረጋል፤ የፓርቲው አባላት መዋጮ በወቅቱና በትክክል መሰብሰቡን ይቆጣጠራል፤   
በ) ኮሚሽኑ ከመካከሉ ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንትና ጸሃፊውን መርጦ ለጉባኤው ያሳውቃል፤ 
ተ) ለፓርቲው ፕሮግራምና ደንብ ተገዢ ያልሆኑ የኮሚሽን አባላትን በ2/3ኛ ድምጽ ያግዳል፣ 
ቸ) ይህን መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በማድረግ የራሱን የአሠራር መመሪያዎች ማውጣት ይችላል፤  
ነ)  የስራ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለጉባዔው ያቀርባል፤ 

6) ኮሚሽኑ በየሶስት ወሩ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል፤ 
7) ኮሚሽኑ የራሱን ዓመታዊ እቅዶች እያዘጋጀ ተግባራቱን ይመራል፤  

አንቀጽ 22. የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት  
1) ጽህፈት ቤቱ ተጠሪነቱ ለፕሬዝዳንቱ ሆኖ የፓርቲውን የፖለቲካ፣ የድርጅት፣ የሕዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። 
2) ጽህፈት ቤቱ ሃላፊና ምክትል ሃላፊ ይኖሩታል፤
 3) ጽህፈት ቤቱ በየወቅቱ እቅድና ሪፖርት አዘጋጅቶ ለፕሬዝዳንቱ ያቀርባል፤ 
4) የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በክልል የቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ አቅራቢነት በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይመደባሉ፤ 
5) የጽህፈት ቤትና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ዝርዝር አሰራርን አስመልክቶ በማዕከላዊ ኮሚቴ መመሪያ ይወጣል፤ 
6)  ጽህፈት ቤቱ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡- 
ሀ) የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዕቅዶች፣ ውሳኔዎችንንና ሌሎች በፕሬዝዳንቱ የሚሰጡ አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ የፓርቲውን ሥራዎች ያቅዳል፣ ያስፈጽማል፣ አፈጻጸሙን ይከታተላል፣ 
ለ) የፓርቲውን ገንዘብ፣ ንብረትና ሰነዶች  በበላይነት ያስተዳድራል፣ በጥንቃቄ እንዲያዙና በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፤ 
ሐ) የአባላት አደረጃጀት፣ የፖለቲካ ግንባታ፣ የህዝብ ግንኙነት፣ የጥናትና ምርምርና ሌሎች ተግባሮችን ይፈፅማል፤ 
መ) በማዕከላዊ ኮሚቴው፣ በስራ አስፈፃሚው ወይም በፕሬዝዳንቱ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት ፓርቲውን ወክሎ ከሶስተኛ ወገኖች ጋር የስራ ግንኙነት ያደርጋል፤ 
ሠ) የጸደቀውን የፓርቲ በጀት ያስተዳድራል፤ 
ረ) የፓርቲውን ፕሮግራም፣ አቅጣጫዎች፣ ሥራ አፈጻጸም እና ዕቅዶችን በሚዲያና የህዝብ ግንኙነት መሳሪያዎች ለህዝብ ያስተዋውቃል፤ 
ሰ) በፓርቲው ስም ውል ይዋዋላል፣ ይከሳል፣ ይከሰሳል፤ 
ሸ) በፓርቲው የሰው ሀይል አስተዳደር መመሪያ መሰረት የጽህፈት ቤቱን ሰራተኞች ይቀጥራል፣ ያስተዳድራል፣ ያሰናብታል፤ 
ቀ) በማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወይም በፕሬዝዳንቱ የሚሰጡ ሌሎች ሥራዎችን ያከናውናል። 

ምዕራፍ  አራት የፓርቲው የክልል ቅርንጫፎች እና የአካባቢ አካላት 

አንቀጽ 23. የፓርቲው የክልል ቅርንጫፎች እና የአካባቢ አካላት አወቃቀር 
1) ብልፅግና ፓርቲ በክልሎች፣ በዞኖች፣ በወረዳዎች፣ በከተሞች እና በቀበሌዎች በየደረጃው አመራር የሚሰጡ የፓርቲ ጉባኤዎች/ኮንፈረንስ፣ የፓርቲ ኮሚቴዎች፣ አስተባባሪ ኮሚቴዎች፣ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽኖች ይኖሩታል፤ 
2) የፌዴራል ተቋማት፣ የፓርላማ መዋቅር፣ የውጪ ጉዳይ፣ የልማት ድርጅቶችና ኢንዱስትሪ ሰራተኞች፣ የምሁራን አደረጃጀቶች በፓርቲው ዋና ጽ/ቤት የሚዋቀሩ ሆነው ዝርዝር መመሪያ ይወጣላቸዋል። 
3) የክልል ጉባዔ፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ እና የቀበሌ የፓርቲ ኮንፈረንሶች በየደረጃው የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ናቸው፣ 
4) የክልል ጉባዔ፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ እና የቀበሌ የፓርቲ ኮንፈረንሶች ውክልናና ስብጥር በማዕከላዊ ኮሚቴ በሚወጣው መመሪያ ይወሰናል፤ 
5) የክልል ጉባዔ እና የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ እና የቀበሌ የፓርቲ ኮንፈረንሶች በየደረጃው በሚገኘው የፓርቲ ኮሚቴ ጠሪነት የሚሰበሰብ ሆኖ፣ የክልል ጉባዔ በየሁለት ዓመት ተኩል አንድ ጊዜ፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ ኮንፈረንሶች በዓመት አንድ ጊዜ፣ የቀበሌ በየስድስት ወሩ ይደረጋል፤ 
6) የፓርቲ የክልል ኮሚቴ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘውና ይህንንም ማዕከላዊ ኮሚቴው ሲፈቅድ አስቸኳይ የክልል ጉባዔ በማንኛውም ጊዜ ሊጠራ ይችላል፤   

አንቀጽ 24. የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ ጉባዔ ተግባርና ኃላፊነት የቅርንጫፍ ፓርቲው የክልል ጉባዔ፤  
1) የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲው ከፍተኛ የአመራር አካል ነው፤ 
  
2) በክልሉ ውስጥ የሚካሄዱን የፓርቲውን አካላት ተግባራት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በፓርቲው ፕሮግራም፣ ደንብ፣ በበላይ የፓርቲ አካላት መመሪያና ውሳኔዎች ላይ በመመርኮዝ ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ውሳኔና አመራር ይሰጣል፤ 
3) የክልሉን የፓርቲ ኮሚቴ አባላትና የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላትን ቁጥር ይወስናል፤ ይመርጣል፤ 
4) የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በሚወስነው ብዛትና ስብጥር መሰረት ለብሔራዊ ጉባዔ ተወካዮችን ይመርጣል፤ 
5)  በክልሉ የፓርቲ ኮሚቴና ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የሚቀርብለትን ሪፖርት ያዳምጣል፣ ይገመግማል፣ ያጸድቃል፤ 
6) የቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ በድምፅ ብልጫ ሲወስን አስቸኳይ የክልል ጉባዔ ሊጠራ ይችላል። 
7) የቅርንጫፍ ፓርቲው ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የክልል ቋሚ ጉባዔ አባላትን 1/3ኛ የድጋፍ ድምፅ ካገኘ አስቸኳይ የክልል ጉባዔ እንዲጠራ ሊያደርግ ይችላል።  
8) ለክልል ጉባዔ የሚያስፈልጉ የዝግጅት ሥራዎች በአስተባባሪ ኮሚቴ እና በቅርንጫፉ ፅ/ቤቱ በሚቋቋም የክልል ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ ይከናወናሉ፤ 
9) የቅርንጫፍ ፓርቲው የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላት በቀጥታ በክልል ጉባዔው ይሳተፋሉ፤ 
10)  ለመደበኛ የክልል ጉባዔ ቢያንስ ከሁለት ወር በፊት ጥሪ መተላለፍና አጀንዳዎቹም መገለጽ አለባቸው፣ አስቸኳይ የክልል ጉባዔ ከአንድ ወር በፊት የጥሪ ጊዜና አጀንዳዎቹ መገለጽ አለባቸው፣  11)  በቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ እና በቁጥጥርና ኢንሰፔክሽን ኮሚሽን አባላት ዕገዳና ስንብት ላይ ውሳኔ ይሰጣል፤ 
12)  የክልል ጉባኤ መደበኛው ሥራውን ከመጀመሩ በፊት በዝግጅት ኮሚቴ የሚቀርብለትን የክልል ጉባዔ ዝግጅት ሪፖርትና የሥነ ሥርዓት ደንብ መርምሮ ያጸድቃል፤ 

አንቀጽ 25. የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ 1) የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለክልሉ ጉባዔና ለማዕከላዊ ኮሚቴ ሆኖ፤ 
  
ሀ) በክልሉ ጉባዔዎች መካከል የክልሉን የፓርቲ እንቅስቃሴ በበላይነት ይመራል፣ 
ለ) የክልል ፓርቲ ኮሚቴ በአስተባባሪ ኮሚቴው ጠሪነት መደበኛ የክልል ጉባዔ ያደርጋል፣ 
ሐ) የክልል ፓርቲ ኮሚቴ የክልል አስተባባሪ ኮሚቴን ብዛት ይወስናል፣ ይመርጣል፤ 
መ) የክልሉን የፓርቲ ኮሚቴ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢን ይመርጣል፣ 
ሠ) የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ በስድስት ወር አንድ ጊዜ ስብሰባ ያካሂዳል፤ 
ረ) የክልሉ የፓርቲ ኮሚቴ ካመነበትና በአስተባባሪ ኮሚቴ ሲፈቀድ ከዚህ ባነሰ ጊዜ ውስጥ አስቸኳይ ኮንፈረንስ ሊጠራ ይችላል። 
2) የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ተግባርና ኃላፊነት 
ሀ) የኮሚቴውን የዕለት ተዕለት ሥራዎች ይመራል፤ 
 ለ) የክልሉን ቅርንጫፍ የፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትን ይመርጣል፤ 
ሐ) የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲዎችን አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ይመድባል፤ 
መ) ፓርቲው ያወጣቸው ፕሮግራሞች፣ አቅጣጫዎች፣ ዕቅዶችና ውሳኔዎች በክልሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፤
 ሠ) የክልሉን የፓለቲካና የድርጅት ሥራዎችን ይመራል፣ 
ረ) በክልሉ ለሚገኙ የፓርቲው አካላት የሥራ አመራር ይሰጣል፣ ይገመግማል፣ ሪፖርት ይቀበላል፤ ሰ) የበላይ አካላትና የክልሉ ቅርንጫፍ ፓርቲ የክልል ጉባዔ ያስተላለፋቸውን መመሪያዎችና ውሳኔዎችን ሥራ ላይ ያውላል፤
 ሸ) አባላት ድርጅታዊ ግዴታቸውን በብቃት መወጣታቸውን ይከታተላል፣ 
ቀ) በየጊዜው ስለስራው እንቅስቃሴ ለፓርቲ ኮሚቴው እና ለፓርቲው ዋና ፅ/ቤት ሪፖርት ያቀርባል፤ 

አንቀጽ 26. የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ 
1) የክልል ቅርንጫፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለክልሉ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ሆኖ፤ 
ሀ) የክልሉን ቅርንጫፍ ፓርቲ የዕለት ተዕለት የፖለቲካና የድርጅት እንቅስቃሴ ይመራል፤ 
ለ) የክልል አስተባባሪ ኮሚቴ በየወሩ አንድ ጊዜ መደበኛ ስብሰባውን ያደርጋል፤ 
  
2) የአስተባባሪ ኮሚቴ ተግባርና ሃላፊነት 
ሀ) ከበላይ አካላት የሚተላለፉ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን በተግባር ያውላል፣ ለሥራው ዝርዝር የአፈጻጸም ፕሮግራም አውጥቶ በክልሉ ቅርንጫፍ የፓርቲ ኮሚቴ ሲፀድቅ በሥራ ላይ ያውላል፤ 
ለ) በቅርንጫፍ ፓርቲ የክልል ጉባዔዎች መካከል የክልሉን የፓርቲ የፖለቲካና የድርጅት ሥራዎች ይመራል፤   
ሐ) የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት ሃላፊንና ምክትል ሃላፊን ይመድባል። 
መ) የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲዎችን የፓርቲ ኮሚቴ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ይመድባል፣ 
ሠ) የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲዎችን ጽ/ቤት ሃላፊና ምክትል ሃላፊ ይመድባል።   
ረ) በክልሉ ውስጥ በየደረጃው የሚገኙ አካላትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ይመራል፣ ያስተባብራል፣ ሪፖርት ይቀበላል፣ ያጠናቅራል፤ 
ሰ) ስለስራው ክንውን ለክልሉ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ሪፖርት ያቀርባል። 

አንቀጽ 27. የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት  
1) ጽህፈት ቤቱ የቅርንጫፍ ፓርቲው የፖለቲካ፣ የድርጅትና የሕዝብ ግንኙነት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።
 2) የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት ተጠሪነቱ ለክልሉ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ እና ለፓርቲው ዋና ፅ/ቤት ይሆናል። 
3) ጽ/ቤቱ ሃላፊና ምክትል ሃላፊ ይኖሩታል። 
4) ጽህፈት ቤቱ በየወቅቱ እቅድና ሪፖርት አዘጋጅቶ ለክልል ፓርቲ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ሰብሳቢው እና ለፓርቲው ዋና ፅ/ቤት ያቀርባል፤ 
5) ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽህፈት ቤቱ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡- 
ሀ) የፓርቲ ኮሚቴውን እና አስተባባሪ ኮሚቴውን ዕቅዶች፣ ውሳኔዎችና በፓርቲው ዋና ፅ/ቤት የሚሰጡ አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ የቅርንጫፍ ፓርቲውን ሥራዎች ያቅዳል፣ ያስፈጽማል፣ አፈጻጸሙን ይከታተላል፣ 
ለ) የቅርንጫፍ ፓርቲውን ገንዘብ፣ ንብረትና ሰነዶች  በበላይነት ያስተዳድራል፣ በጥንቃቄ እንዲያዙና በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፤ 
  
ሐ) የአባላት አደረጃጀት፣ የፖለቲካ ግንባታ፣ የህዝብ ግንኙነትና ሌሎች ተግባሮችን ይፈፅማል፤ 
መ) በቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴው፣ በአስተባባሪው ወይም በሰብሳቢው በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት ፓርቲውን ወክሎ በክልል ደረጃ ከሶስተኛ ወገኖች ጋር ይገናኛል፤ 
ሠ) የፓርቲውን ፕሮግራም፣ አቅጣጫዎች፣ ሥራ አፈጻጸም እና ዕቅዶችን በሚዲያና የህዝብ ግንኙነት መሳሪያዎች ለህዝብ ያስተዋውቃል፤ 
ረ) በቅርንጫፍ ፓርቲው ስም ውል ይዋዋላል፣ ይከሳል፣ ይከሰሳል፤ 
ሰ) በፓርቲው የሰው ሀይል አስተዳደር መመሪያ መሰረት የጽህፈት ቤቱን ሰራተኞች ይቀጥራል፣ ያስተዳድራል፣ ያሰናብታል፤ 
ሸ) በቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ፣ በአስተባባሪ ኮሚቴ ወይም በሰብሳቢው የሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል።

አንቀጽ 28. የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ 
1) በዞኑ ውስጥ የሚካሄዱትን የፓርቲውን አካላት ተግባራት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በፓርቲው ፕሮግራም፣ ደንብ፣ በበላይ የፓርቲ አካላት መመሪያና ውሳኔዎች ላይ በመመርኮዝ ከዞኑ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ውሳኔና አመራር ይሰጣል፤ 
2) የዞኑን ቅርንጫፍ የፓርቲ ኮሚቴ አባላትና የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላትን ቁጥር ይወስናል፤ ይመርጣል፤ 
3) የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ የክልል ጉባዔ በሚወስነው ብዛትና ስብጥር መሰረት የክልል ጉባዔ ተወካዮችን ይመርጣል፤ 
4) በዞኑ የፓርቲ ኮሚቴና ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የሚቀርብለትን ሪፖርት ያዳምጣል፣ ይገመግማል፣ ያጸድቃል፤ 

አንቀጽ 29. የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ 1) የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለዞኑ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ ሆኖ፤ 
ሀ) በዞኑ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንሶች መካከል የዞኑን ቅርንጫፍ ፓርቲ እንቅስቃሴ በበላይነት ይመራል፣ 
  
ለ) የዞኑ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ በአስተባባሪ ኮሚቴው ጠሪነት መደበኛ ኮንፈረንሶችን ያደርጋል፣ መ) የዞን ፓርቲ ኮሚቴ በሶስት ወር አንድ ጊዜ ስብሰባ ያደርጋል፤ 
ሠ) የዞኑ የፓርቲ ኮሚቴ ካመነበትና በአስተባባሪ ኮሚቴ ሲፈቀድ ከዚህ ባነሰ ጊዜ ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል።
 2) የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ተግባርና ሃላፊነት
 ሀ) የኮሚቴውን የዕለት ተዕለት ሥራዎች ይመራል፤  
ለ) የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲዎችን አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ይመድባል፤ 
ሐ) ፓርቲው ያወጣቸውን አቅጣጫዎች፣ ዕቅዶችና ውሳኔዎች በዞኑ ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ መ) የዞኑን የፓለቲካና የድርጅት ሥራዎችን ይመራል፣ 
ሠ) በዞኑ ለሚገኙ የፓርቲው አካላት የሥራ አመራር ይሰጣል፣ ይገመግማል፣ ሪፖርት ይቀበላል፤ 
ረ) የበላይ አካላትና የዞኑ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ ያስተላለፋቸውን መመሪያዎችና ውሳኔዎችን ሥራ ላይ ያውላል፤ 
ሰ) አባላት ድርጅታዊ ግዴታቸውን በብቃት መወጣታቸውን ይከታተላል፣ 
ሸ) በየጊዜው ስለስራው እንቅስቃሴ ለዞኑ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስና ለክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሪፖርት ያቀርባል፤ 

አንቀጽ 30. የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ 
1) የዞን ቅርንጫፍ የፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለዞኑ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ፣ ለክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሆኖ፤ 
ሀ) የዞኑን ቅርንጫፍ ፓርቲ የዕለት ተዕለት የፖለቲካና የድርጅት እንቅስቃሴዎችን ይመራል፤ 
ለ) የዞን አስተባባሪ ኮሚቴ በየ15 ቀኑ ስብሰባ ያደርጋል፤ 2
) የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ተግባርና ሃላፊነት  
ሀ) ከበላይ አካላት የሚተላለፉ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን በተግባር ያውላል፣ ለሥራው ዝርዝር የአፈጻጸም ፕሮግራም አውጥቶ በዞኑ ቅርንጫፍ የፓርቲ ኮሚቴ ሲፀድቅ በሥራ ላይ ያውላል፤ 
  
ለ) በኮሚቴ ኮንፈረንሶች መካካል የዞኑን የፓርቲ የፖለቲካና የድርጅት ሥራዎች ይመራል፤ 
ሐ) በዞኑ ውስጥ በየደረጃው የሚገኙ አካላትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ይመራል፣ ያስተባብራል፣ ሪፖርት ይቀበላል፣ ይገመግማል። 
መ) የወረዳን ቅርንጫፍ ፓርቲዎችን ኮሚቴ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ይመድባል፣ 
ሠ) የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤቶችን ሃላፊና ምክትል ሃላፊን ይመድባል። 
ረ) ስለስራው ክንውን ለዞኑ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴና ለክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት ሪፖርት ያቀርባል። 

አንቀጽ 31. የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት  
1) ጽህፈት ቤቱ የቅርንጫፍ ፓርቲው የፖለቲካ፣ የድርጅትና የሕዝብ ግንኙነት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። 
2) የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት ተጠሪነቱ ለዞኑ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ እና ለክልል ቅርንጫፍ ፓርቲው ፅ/ቤት ይሆናል። 
3) ጽ/ቤቱ ሃላፊና ምክትል ሃላፊ ይኖሩታል። 
4) ጽህፈት ቤቱ በየወቅቱ እቅድና ሪፖርት አዘጋጅቶ ለዞን ፓርቲ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ሰብሳቢው እና ለክልል ቅርንጫፍ ፓርቲው ፅ/ቤት ያቀርባል፤ 
5) ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽህፈት ቤቱ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡- 

ሀ) የፓርቲ ኮሚቴውን እና አስተባባሪ ኮሚቴውን ዕቅዶች፣ ውሳኔዎችና በክልል ቅርንጫፍ ፓርቲው ፅ/ቤት የሚሰጡ አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ የቅርንጫፍ ፓርቲውን ሥራዎች ያቅዳል፣ ያስፈጽማል፣ አፈጻጸሙን ይከታተላል፣ 
ለ) የቅርንጫፍ ፓርቲውን ገንዘብ፣ ንብረትና ሰነዶች  በበላይነት ያስተዳድራል፣ በጥንቃቄ እንዲያዙና በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፤ 
ሐ) የአባላት አደረጃጀት፣ የፖለቲካ ግንባታ፣ የህዝብ ግንኙነትና ሌሎች ተግባሮችን ይፈፅማል፤ 
  
መ) በቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴው፣ በአስተባባሪው ወይም በሰብሳቢው በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት ፓርቲውን ወክሎ በዞን ደረጃ ከሶስተኛ ወገኖች ጋር ይገናኛል፤ 
ሠ) የፓርቲውን ፕሮግራም፣ አቅጣጫዎች፣ ሥራ አፈጻጸም እና ዕቅዶችን በሚዲያና የህዝብ ግንኙነት መሳሪያዎች ለህዝብ ያስተዋውቃል፤ 
ረ) በቅርንጫፍ ፓርቲው ስም ውል ይዋዋላል፣ ይከሳል፣ ይከሰሳል፤ 
ሰ) በፓርቲው የሰው ሀይል አስተዳደር መመሪያ መሰረት የጽህፈት ቤቱን ሰራተኞች ይቀጥራል፣ ያስተዳድራል፣ ያሰናብታል፤ 
ሸ) በቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ፣ በአስተባባሪ ኮሚቴ ወይም በሰብሳቢው የሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል። 

አንቀጽ 32. የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ 
1) በወረዳ ውስጥ የሚካሄዱትን የፓርቲውን አካላት ተግባራት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በፓርቲው ፕሮግራም፣ ደንብ፣ በበላይ የፓርቲ አካላት መመሪያና ውሳኔዎች ላይ በመመርኮዝ ከወረዳ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ውሳኔና አመራር ይሰጣል፤ 
2) የወረዳውን ቅርንጫፍ የፓርቲ ኮሚቴ አባላትና የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላትን ቁጥር ይወስናል፤ ይመርጣል፤ 
3) የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ በሚወስነው ብዛትና ስብጥር መሰረት ለዞን ቅርንጫፍ ኮንፈረንስ ተወካዮችን ይመርጣል፤ 
4) በወረዳው የፓርቲ ኮሚቴና ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የሚቀርብለትን ሪፖርት ያዳምጣል፣ ይገመግማል፣ ያጸድቃል፤ 

አንቀጽ 33. የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ
1) የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለወረዳው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ ሆኖ፤
 ሀ) በወረዳው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንሶች መካከል የወረዳውን ቅርንጫፍ ፓርቲ እንቅስቃሴ በበላይነት ይመራል፣ 
  
ለ) የወረዳው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ በአስተባባሪ ኮሚቴው ጠሪነት መደበኛ ኮንፈረንስ ያደርጋል፣ ሐ) የወረዳውን ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ይመርጣል፣ 
መ) የወረዳውን ፓርቲ ኮሚቴ በሶስት ወር አንድ ጊዜ ስብሰባ ያደርጋል፤ 
ሠ) የወረዳ የፓርቲ ኮሚቴ ካመነበትና በአስተባባሪ ኮሚቴ ሲፈቀድ ከዚህ ባነሰ ጊዜ ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል። 
2) የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ተግባርና ሃላፊነት 
ሀ) የኮሚቴውን የዕለት ተዕለት ሥራዎች ይመራል፤  
ለ) የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲዎችን አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ይመድባል፤ 
ሐ) ፓርቲው ያወጣቸውን አቅጣጫዎች፣ ዕቅዶችና ውሳኔዎች በወረዳው ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ 
መ) የወረዳውን የፓለቲካና የድርጅት ሥራዎችን ይመራል፣ 
ሠ) በወረዳው ለሚገኙ የፓርቲው አካላት የሥራ አመራር ይሰጣል፣ ይገመግማል፣ ሪፖርት ይቀበላል፤ ረ) የበላይ አካላትና የወረዳው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ ያስተላለፋቸውን መመሪያዎችና ውሳኔዎችን ሥራ ላይ ያውላል፤ 
ሰ) አባላት ድርጅታዊ ግዴታቸውን በብቃት መወጣታቸውን ይከታተላል፣ 
ሸ) በየጊዜው ስለስራው እንቅስቃሴ ለወረዳው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስና ለዞኑ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሪፖርት ያቀርባል፤ 

አንቀጽ 34. የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ 
1. የወረዳ ቅርንጫፍ የፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለወረዳው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ፣ ለዞን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሆኖ፤ 
ሀ) የወረዳውን ቅርንጫፍ ፓርቲ የዕለት ተዕለት የፖለቲካና የድርጅት እንቅስቃሴዎችን ይመራል፤ ለ) የወረዳ አስተባባሪ ኮሚቴ በየ15 ቀኑ ስብሰባ ያደርጋል፤
 2. የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ተግባርና ሃላፊነት  
ሀ) ከበላይ አካላት የሚተላለፉ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን በተግባር ያውላል፣ ለሥራው ዝርዝር የአፈጻጸም ፕሮግራም አውጥቶ በወረዳው ቅርንጫፍ የፓርቲ ኮሚቴ ሲፀድቅ በሥራ ላይ ያውላል፤ 
  
ለ) በኮሚቴ ኮንፈረንሶች መካካል የወረዳውን የፓርቲ የፖለቲካና የድርጅት ሥራዎች ይመራል፤ 
ሐ) በወረዳ ውስጥ በየደረጃው የሚገኙ አካላትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ይመራል፣ ያስተባብራል፣ ሪፖርት ይቀበላል፣ ይገመግማል። 
መ) የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴዎችን ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ይመድባል፣ 
ሠ) የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤቶችን ሃላፊና ምክትል ሃላፊን ይመድባል። 
ረ) ስለስራው ክንውን ለወረዳው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴና ለዞን ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት ሪፖርት ያቀርባል።  

አንቀጽ 35. የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት  
1. ጽህፈት ቤቱ የቅርንጫፍ ፓርቲው የፖለቲካ፣ የድርጅትና የሕዝብ ግንኙነት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።
 2. የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት ተጠሪነቱ ለወረዳው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ እና ለዞን ቅርንጫፍ ፓርቲው ፅ/ቤት ይሆናል። 
3. ጽ/ቤቱ ሃላፊና ምክትል ሃላፊ ይኖሩታል። 
4. ጽህፈት ቤቱ በየወቅቱ እቅድና ሪፖርት አዘጋጅቶ ለወረዳ ፓርቲ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ሰብሳቢው እና ለዞን ቅርንጫፍ ፓርቲው ፅ/ቤት ያቀርባል፤ 
5. ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽህፈት ቤቱ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡- 

ሀ) የፓርቲ ኮሚቴውን እና አስተባባሪ ኮሚቴውን ዕቅዶች፣ ውሳኔዎችና በዞን ቅርንጫፍ ፓርቲው ፅ/ቤት የሚሰጡ አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ የቅርንጫፍ ፓርቲውን ሥራዎች ያቅዳል፣ ያስፈጽማል፣ አፈጻጸሙን ይከታተላል፣ 
ለ) የቅርንጫፍ ፓርቲውን ገንዘብ፣ ንብረትና ሰነዶች  በበላይነት ያስተዳድራል፣ በጥንቃቄ እንዲያዙና በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፤ 
ሐ) የአባላት አደረጃጀት፣ የፖለቲካ ግንባታ፣ የህዝብ ግንኙነትና ሌሎች ተግባሮችን ይፈፅማል፤ 
  
መ) በቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴው፣ በአስተባባሪው ወይም በሰብሳቢው በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት ፓርቲውን ወክሎ በወረዳ ደረጃ ከሶስተኛ ወገኖች ጋር ይገናኛል፤ 
ሠ) የፓርቲውን ፕሮግራም፣ አቅጣጫዎች፣ ሥራ አፈጻጸም እና ዕቅዶችን በሚዲያና የህዝብ ግንኙነት መሳሪያዎች ለህዝብ ያስተዋውቃል፤ 
ረ) በቅርንጫፍ ፓርቲው ስም ውል ይዋዋላል፣ ይከሳል፣ ይከሰሳል፤ 
ሰ) በፓርቲው የሰው ሀይል አስተዳደር መመሪያ መሰረት የጽህፈት ቤቱን ሰራተኞች ይቀጥራል፣ ያስተዳድራል፣ ያሰናብታል፤ 
ሸ) በቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ፣ በአስተባባሪ ኮሚቴ ወይም በሰብሳቢው የሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል። 

አንቀጽ 36. የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ 
1. በቀበሌ ውስጥ የሚካሄዱትን የፓርቲውን አካላት ተግባራት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በፓርቲው ፕሮግራም፣ ደንብ፣ በበላይ የፓርቲ አካላት መመሪያና ውሳኔዎች ላይ በመመርኮዝ ከቀበሌው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ውሳኔና አመራር ይሰጣል፤ 
2. የቀበሌውን ቅርንጫፍ የፓርቲ ኮሚቴ አባላትና የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላትን ቁጥር ይወስናል፤ ይመርጣል፤ 
3. የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ በሚወስነው ብዛትና ስብጥር መሰረት ለወረዳ ቅርንጫፍ ኮንፈረንስ ተወካዮችን ይመርጣል፤ 
4. በቀበሌው የፓርቲ ኮሚቴና ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የሚቀርብለትን ሪፖርት ያዳምጣል፣ ይገመግማል፣ ያጸድቃል፤ 

አንቀጽ 37. የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ 
1. የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለቀበሌው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ ሆኖ፤ 
ሀ) በቀበሌው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንሶች መካከል የቀበሌውን ቅርንጫፍ ፓርቲ እንቅስቃሴ በበላይነት ይመራል፣ 
ለ) የቀበሌው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ በአስተባባሪ ኮሚቴው ጠሪነት መደበኛ ኮንፈረንስ ያደርጋል፣ 
  
ሐ) የቀበሌውን ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ይመርጣል፣ 
ረ) የቀበሌውን ፓርቲ ኮሚቴ በየወሩ አንድ ጊዜ ስብሰባ ያደርጋል፤
 ሰ) የቀበሌ የፓርቲ ኮሚቴ ካመነበትና በአስተባባሪ ኮሚቴ ሲፈቀድ ከዚህ ባነሰ ጊዜ ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል።
 2. የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ ተግባርና ሃላፊነት
 ሀ) የፓርቲ ኮሚቴውን የዕለት ተዕለት ሥራዎች ይመራል፤  
ለ) ፓርቲው ያወጣቸውን አቅጣጫዎች፣ ዕቅዶችና ውሳኔዎች በቀበሌው ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ 
ሐ) የቀበሌውን የፓለቲካና የድርጅት ሥራዎችን ይመራል፣ 
መ) በቀበሌው ለሚገኙ የፓርቲው አካላት የሥራ አመራር ይሰጣል፣ ይገመግማል፣ ሪፖርት ይቀበላል፤ ሠ) የበላይ አካላትና የቀበሌው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ ያስተላለፋቸውን መመሪያዎችና ውሳኔዎችን ሥራ ላይ ያውላል፤ 
ረ) አባላት ድርጅታዊ ግዴታቸውን በብቃት መወጣታቸውን ይከታተላል፣ 
ሰ) በየጊዜው ስለስራው እንቅስቃሴ ለቀበሌው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስና ለወረዳው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሪፖርት ያቀርባል፤ 

አንቀጽ 38. የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ 
1. የቀበሌ ቅርንጫፍ የፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለቀበሌው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ፣ ለወረዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሆኖ፤ 
ሀ) የቀበሌውን ቅርንጫፍ ፓርቲ የዕለት ተዕለት የፖለቲካና የድርጅት እንቅስቃሴዎችን ይመራል፤ ለ) የቀበሌ አስተባባሪ ኮሚቴ በየ15 ቀኑ ስብሰባ ያደርጋል፤ 
2. የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ተግባርና ሃላፊነት  
ሀ) ከበላይ አካላት የሚተላለፉ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን በተግባር ያውላል፣ ለሥራው ዝርዝር የአፈጻጸም ፕሮግራም አውጥቶ በቀበሌው ቅርንጫፍ የፓርቲ ኮሚቴ ሲፀድቅ በሥራ ላይ ያውላል፤
 ለ) በኮሚቴ ኮንፈረንሶች መካካል የቀበሌውን የፓርቲ የፖለቲካና የድርጅት ሥራዎች ይመራል፤ 
  
ሐ) በቀበሌ ውስጥ በየደረጃው የሚገኙ አካላትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ይመራል፣ ያስተባብራል፣ ሪፖርት ይቀበላል፣ ይገመግማል። 
መ) ስለስራው ክንውን ለቀበሌው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴና ለወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት ሪፖርት ያቀርባል።
  
አንቀጽ 39. የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት  
1) ጽህፈት ቤቱ የቅርንጫፍ ፓርቲው የፖለቲካ፣ የድርጅትና የሕዝብ ግንኙነት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል፣ 
2) የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት ተጠሪነቱ ለቀበሌው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ እና ለወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲው ፅ/ቤት ይሆናል፣ 
3) ጽ/ቤቱ ሃላፊ ይኖረዋል፣ 
4) ጽህፈት ቤቱ በየወቅቱ እቅድና ሪፖርት አዘጋጅቶ ለቀበሌ ፓርቲ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ሰብሳቢው እና ለወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲው ፅ/ቤት ያቀርባል፤
 5) ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽህፈት ቤቱ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡- 
ሀ) የፓርቲ ኮሚቴውን እና አስተባባሪ ኮሚቴውን ዕቅዶች፣ ውሳኔዎችና በወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲው ፅ/ቤት የሚሰጡ አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ የቅርንጫፍ ፓርቲውን ሥራዎች ያቅዳል፣ ያስፈጽማል፣ አፈጻጸሙን ይከታተላል፣ 
ለ) የቅርንጫፍ ፓርቲውን ገንዘብ፣ ንብረትና ሰነዶች  በበላይነት ያስተዳድራል፣ በጥንቃቄ እንዲያዙና በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፤ 
ሐ) የአባላት አደረጃጀት፣ የፖለቲካ ግንባታ፣ የህዝብ ግንኙነትና ሌሎች ተግባሮችን ይፈፅማል፤ 
መ) በቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴው፣ በአስተባባሪው ወይም በሰብሳቢው በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት ፓርቲውን ወክሎ በቀበሌ ደረጃ ከሶስተኛ ወገኖች ጋር ይገናኛል፤ 
  
ሠ) የፓርቲውን ፕሮግራም፣ አቅጣጫዎች፣ ሥራ አፈጻጸም እና ዕቅዶችን በሚዲያና የህዝብ ግንኙነት መሳሪያዎች ለህዝብ ያስተዋውቃል፤ 
ረ) በቅርንጫፍ ፓርቲው ስም ውል ይዋዋላል፣ ይከሳል፣ ይከሰሳል፤ 
ሰ) በቅርንጫፍ ፓርቲ ኮሚቴ፣ በአስተባባሪ ኮሚቴ ወይም በሰብሳቢው የሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል። 

አንቀጽ 40. የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የክልል የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለክልሉ ቅርንጫፍ ፓርቲ የክልል ጉባዔ ሆኖ የሚከተሉትን ተግባሮች ያከናውናል፣ 
ሀ) አባላትና ዕጩ አባላት የፓርቲውን ፕሮግራም፣ ደንብ፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ማክበራቸውን፣ ለጥብቅ ዲስፕሊን ተገዢ መሆናቸውን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፤ 
ለ) የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲው የክልል ጉባዔ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በአግባቡ መፈፀማቸውን ይከታተላል፣ 
ሐ) የፓርቲውን ጥራትና ጥንካሬ ለማዳበር አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል፤ 
መ) ከአባሉ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች ይቀበላል፣ ይመረምራል፣ 
ሠ) የክልሉ አመራር አካላትና የስራ ዘርፎች የሰነድ አያያዝና አሠራር ይቆጣጠራል፤ 
ረ) የፓርቲ ገንዘብ፣ ሰነዶችና ንብረት በክልሉ በአግባቡ መጠበቁንና አገልግሎት ላይ መዋሉን ይቆጣጠራል፤ 
ሰ) በክልሉ አባላት መዋጮ በወቅቱና በትክክል መሰብሰቡን ይቆጣጠራል፤
 ሸ) ስለሥራው አፈጻጸም ለክልል ቅርንጫፍ ፓርቲው የክልል ጉባዔ ሪፖርት ያቀርባል፤ 

አንቀጽ 41. የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የዞን የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለዞኑ ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ ሆኖ የሚከተሉትን ተግባሮች ያከናውናል፣ 
  
ሀ) አባላትና ዕጩ አባላት የፓርቲውን ፕሮግራም፣ ደንብ፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ማክበራቸውን፣ ለጥብቅ ዲስፕሊን ተገዢ መሆናቸውን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፤ 
ለ) የዞን ቅርንጫፍ ፓርቲው ኮንፈረንስ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በአግባቡ መፈፀማቸውን ይከታተላል፣ 
ሐ) የፓርቲውን ጥራትና ጥንካሬ ለማዳበር አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል፤ 
መ) ከአባሉ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች ይቀበላል፣ ይመረምራል፣ 
ሠ) የዞኑ አመራር አካላትና የስራ ዘርፎች የሰነድ አያያዝና አሠራር ይቆጣጠራል፤ 
ረ) የፓርቲ ገንዘብ፣ ሰነዶችና ንብረት በዞኑ በአግባቡ መጠበቁንና አገልግሎት ላይ መዋሉን ይቆጣጠራል፤ 
ሰ) በዞኑ አባላት መዋጮ በወቅቱና በትክክል መሰብሰቡን ይቆጣጠራል፤ 
ሸ) ስለሥራው አፈጻጸም ለዞን ቅርንጫፍ ፓርቲው ኮንፈረንስ ሪፖርት ያቀርባል፤ 

አንቀጽ 42. የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የወረዳ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለወረዳው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ ሆኖ የሚከተሉትን ተግባሮች ያከናውናል፣ 
ሀ) አባላትና ዕጩ አባላት የፓርቲውን ፕሮግራም፣ ደንብ፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ማክበራቸውን፣ ለጥብቅ ዲስፕሊን ተገዢ መሆናቸውን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፤ 
ለ) የወረዳ ቅርንጫፍ ፓርቲው ኮንፈረንስ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በአግባቡ መፈፀማቸውን ይከታተላል፣ 
ሐ) የፓርቲውን ጥራትና ጥንካሬ ለማዳበር አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል፤
 መ) ከአባሉ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች ይቀበላል፣ ይመረምራል፣ 
ሠ) የወረዳው አመራር አካላትና የስራ ዘርፎች የሰነድ አያያዝና አሠራር ይቆጣጠራል፤ 
ረ) የፓርቲ ገንዘብ፣ ሰነዶችና ንብረት በወረዳው በአግባቡ መጠበቁንና አገልግሎት ላይ መዋሉን ይቆጣጠራል፤ 
ሰ) በወረዳው አባላት መዋጮ በወቅቱና በትክክል መሰብሰቡን ይቆጣጠራል፤ 
ሸ) ስለሥራው አፈጻጸም ለወረዳው ቅርንጫፍ ፓርቲው ኮንፈረንስ ሪፖርት ያቀርባል፤ 
  
አንቀጽ 43. የቀበሌ ቅርንጫፍ ፓርቲ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የቀበሌ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለቀበሌው ቅርንጫፍ ፓርቲ ኮንፈረንስ ሆኖ የሚከተሉትን ተግባሮች ያከናውናል፣ 
ሀ) አባላትና ዕጩ አባላት የፓርቲውን ፕሮግራም፣ ደንብ፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ማክበራቸውን፣ ለጥብቅ ዲስፕሊን ተገዢ መሆናቸውን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፤ 
ለ) የቅርንጫፍ ፓርቲው ኮንፈረንስ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በአግባቡ መፈፀማቸውን ይከታተላል፣ ሐ) የፓርቲውን ጥራትና ጥንካሬ ለማዳበር አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል፤ 
መ) ከአባሉ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች ይቀበላል፣ ይመረምራል፣
 ሠ) የቀበሌው አመራር አካላትና የስራ ዘርፎች የሰነድ አያያዝና አሠራር ይቆጣጠራል፤
 ረ) የፓርቲ ገንዘብ፣ ሰነዶችና ንብረት በቀበሌው በአግባቡ መመጠበቁንና አገልግሎት ላይ መዋሉን ይቆጣጠራል፤ 
ሰ) በቀበሌው የአባላት መዋጮ በወቅቱና በትክክል መሰብሰቡን ይቆጣጠራል፤ 
ሸ) ስለሥራው አፈጻጸም ለቀበሌው ቅርንጫፍ ፓርቲው ኮንፈረንስ ሪፖርት ያቀርባል፤ 

ምዕራፍ  አምስት ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች 

አንቀፅ 44፤ የስልጣን ገደብ 
1. የፓርቲው ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንትን ጨምሮ የሃላፊነት ዘመን ቆይታን የሚገድብ ዝርዝር መመሪያ በማዕከላዊ ኮሚቴ ይወጣል። 
2. በእያንዳንዱ መደበኛ ጉባዔና ኮንፈረንስ ወቅት ከሚመረጡ ጉባዔተኞች እና የኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ውስጥ ቢያንስ 30% አዲስ መሆን ይኖርባቸዋል። 
3. የአባልነት የእድሜ ጣሪያን እና የክብር አባልነትን የተመለከተ ዝርዝር አፈፃፀም በማዕከላዊ ኮሚቴው ይወጣል። 
  
አንቀጽ 45. የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎች 
1) ቀደም ሲል ህጋዊ ሰውነት ኖሯቸው በተናጠል የተደራጁት አባልና አጋር ድርጅቶች ህጋዊ ሰውነታቸውን ያከስማሉ፤ 
2) የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች የነበራቸውን የተናጠል መብትና ግዴታዎች ወደ አዲሱ ፓርቲ ያስተላልፋሉ፤ 

አንቀጽ 46. የፓርቲው  የፋይናንስ ምንጮች የፓርቲው የፋይናንስ ምንጮች ከአባላት መዋጮ፣ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ከፓርቲው ደጋፊዎች እና ወዳጆች ከሚገኝ ድጋፍ ይሆናል።

አንቀጽ 47. የፓርቲው የሰው ኃብት፣ ፋይናንስና የሂሳብ መዛግብት የአሰራር ሥርዓት 
1) የፓርቲው የሰው ኃብት፣ ፋይናንስና ንብረት ማዕከላዊ ኮሚቴ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት የሚተዳደር ይሆናል፤ 
2) ፓርቲው የተሟሉና ትክክለኛ የሂሳብ መዛግብት ይይዛል፣ በውስጥና በውጭ ኦዲተር በየዓመቱ ያስመረምራል፡፡ 

አንቀጽ 48. በፓርቲው ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች አፈታት ሥርዓት 
1) በፓርቲው አካላት ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባበቶች በዚህ ደንብ ውስጥ በተደነገጉ የአሰራር ሥርዓት መፈታት አለባቸው፣ 
2) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ (1) መሰረት መፈታት ካልቻለ በአገሪቱ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር ሕግና በሌሎች ሕጎች መሰረት ይፈታል፡፡    

አንቀጽ 49. የፓርቲ መፍረስ የፓርቲው ብሔራዊ አስቸኳይ ጉባዔ ቢያንስ በሶስት አራተኛ(3/4) ድምጽ ፓርቲው እንዲፈርስ ሊወስን ይችላል፡፡ 

አንቀጽ 50. የፓርቲው አማካሪ የመማክርት ጉባዔ 
1) ፓርቲው የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማዎቹን ለማሳካት ከተለያዩ ሙያ ያላቸው ምሁራኖችና ታዋቂ ግለሰቦችን ያቀፈ የፓርቲው መማክርት ጉባዔ በፕሬዚዳንቱ አቅራቢነት በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊቋቋም ይችላል። 
  
2) የዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀጽ (1) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በክልሉ የፓርቲ ሰብሳቢ አቅራቢነት የክልል አስተባባሪ ኮሚቴ የመማክርት ጉባዔ ሊያቋቋሙ ይችላሉ፡፡ 

አንቀጽ 51. የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ የበላይነት 
1) መተዳደሪያ ደንቡ የፓርቲው የበላይ ሕግ በመሆኑ ደንቡና የደንቡ ድንጋጌዎች በሙሉ በፓርቲው አካላትና አባላት ላይ አስገዳጅነት ይኖረቸዋል፡፡ 
2) በመተዳደሪያ ደንቡና በሌሎች የፓርቲ ሰነዶች መካከል ግጭት ሲያጋጥም የዚህ መተዳደሪያ ደንብ ድንጋጌዎች የበላይነት ይኖራቸዋል። 

አንቀጽ 52. መመሪያ የማውጣት ሥልጣን በዚህ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ለተለያዩ አካላት የተሠጠው ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ይህን ደንብ ሥራ ላይ ለማዋል የሚያግዙ መመሪያዎችን ሊያወጣ ይችላል። 

አንቀጽ 53.  መተዳደሪያ ደንቡን ማሻሻል፣ መቀየር እና ስለመሻር 
1) ይህን መተዳደሪያ ደንብ ሊያሻሽል፣ ሊቀይርና ሊሽር የሚችለው የፓርቲው ብሔራዊ ጉባዔ ብቻ ነው፤ 
2) የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተደነገገው እንደተጠቀ ሆኖ፤ የመተዳደሪያ ደንቡ የማሻሻያ ሃሳብ ሊቀርብ የሚችለው፦ 
ሀ) በፕሬዝዳንቱ 
ለ) በማዕከላዊ ኮሚቴው 1/3 ድምጽ ድጋፍ ሲያገኝ 
ሐ) በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አብላጫ ድምጽ ድጋፍ ሲያገኝ 
3) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) መሠረት የቀረበ የማሻሻያ ሃሳብ ለብሔራዊ ጉባዔ መቅረብ የሚችለው በማዕከላዊ ኮሚቴው በአብላጫ ድምጽ ድጋፍ ካገኘ ነው።
 4) በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀጽ (3) መሠረት በማዕከላዊ ኮሚቴ የቀረበውን የማሻሻያ ሀሳብ የብሔራዊ ጉባኤ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቅ ይኖርበታል። 

አንቀጽ 54. መተዳደሪያ ደንቡ ስለሚጸናበት ይህ መተዳደሪያ ደንብ በፓርቲው መሥራች ጉባኤ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል። 

ጥቅምት 2012 ዓ.ም

Comments

Popular posts from this blog

የደመወዝ ስኬል አፈጻጸም መመሪያ

በዜሮ ዓመት የወጣ ክፍት የስራ ማስታወቂያ

የነጥብ ስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት