የደመወዝ ስኬል አፈጻጸም መመሪያ

የነጥብ የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት
የደመወዝ ስኬል አፈጻጸም መመሪያ
-------------------------------------
Image may contain: text

ትርጉም

1. «የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ» ማለት የአንድን ሠራተኛ ደመወዝ ወደ አዲሱ የደመወዝ ስኬል ለማሸጋገር ሲባል ቅርበቱ እየታየ የነበረውን ደመወዝ እንደሁኔታው ወደ አዲሱ የደመወዝ ስኬል የመነሻ፣ የእርከን ወይም የጣሪያ ደመወዝ ላይ ለማሳረፍ የሚፈቅድ የደመወዝ ማስተካከያ ነው።
2. የመሸጋገሪያ ደመወዝ» ማለት በዚህ መመሪያ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 3 (ለ) መሠረት አንድ ሠራተኛ በደመወዝ ስኬል ሽግግሩ የሚያገኘውን የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ መጠን ለሶስት በማካፈል መደበኛ ደመወዙ ላይ ጨምሮ እስከ ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ድረስ የሚከፈል ደመወዝ ነው፡፡
የመመሪያው የተፈጻሚነት ወሰን
-----------------------------
ይህ መመሪያ ተግባራዊ የሚደረገው የሥራ መደቦቻቸው በነጥብ የሥራ ምዘና ዘዴ ተመዝነው ደረጃ በወጣላቸው የሥራ መደቦች ላይ ለተደለደሉ ሠራተኞች ብቻ ነው፡፡
ልዩ ልዩ ውሳኔዎች
-----------------------
1) በሥራ ላይ የሚውለው የደመወዝ ስኬል
የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት እና የመንግስት የመክፈል አቅም ከግምት ውስጥ ገብቶ የተቀረጸውና በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተወሰነውና በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ በፀደቀው መሰረት የደመወዝ ስኬል በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተግባራዊ ይሆናል፡፡ /የዚህ መመሪያ አባሪ ሆኖ ተያይዟል፡፡
2) ወደፊት ልዩ የደመወዝ ስኬል የማይፈቀድ ስለመሆኑ
የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት በሀገር አቀፍ ደረጃ መተግበርን ተከትሎ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያሉ የደመወዝ ስኬሎችን ወደ አንድ የማሰባሰብ ተግባርና ሥርዓቱ ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ጸንቶ መጠበቅ ስላለበት መንግሥት አገር አቀፍ የደመወዝ ስኬል መዘርጋት ሥርዓትን የልዩ የደመወዝ ስኬል ይፈቀድልኝ የሚሸረሽር ጥያቄን የማያስተናግድ ስለመሆኑ በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ የተላለፈው ውሳኔ የጸና ሆኖ ተግባራዊ ይሆናል፡፡
3) ተጨማሪ ወጪውን በሶስት የበጀት ዓመታት ስለመሸፈን
 ከነባሩ የሥራዎች ምዘና ስርዓት ወደ ነጥብ የሥራዎች ምዘና ዘዴ የሚደረገው ሽግግር ዓላማ ለሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ ወይም ጭማሪ ማድረግ አይደለም፡፡ ሆኖም ሽግግሩ በአንዳንድ የሥራ መደቦች ላይ የደመወዝ ለውጥ ስለሚያስከትል በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ የሚኖረውን የወጪ ጫና ከአስተዳደሩ የመክፈል አቅም ጋር ተገናዝቦ በመቋቋም የደመወዝ ስኬል ሽግግሩን ቀለል ባለ መንገድ ለመፈጸም ዝርዝር የአከፋፈል ሁኔታው፡-
ሀ) በተደለደሉበት የሥራ መደብ ብር 1,000 እና ከዚህ በታች የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ የሚያገኙ ሠራተኞች ሙሉ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያውን በአንድ ጊዜ እንዲያገኙ፣
ለ) ከብር 1,000 በላይ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ የሚያገኙ ሠራተኞች ልዩነቱን በሶስት እኩል ክፍያዎች እንዲጠናቀቅላቸው ይደረጋል፡፡
በዚህ ጥናት ያልተካተተ ተቋም
----------------------------
የአስተዳደሩ ገቢዎች ባለስልጣን ከደመወዝ ስኬል ሽግግር ውሳኔ በፊት ተፈቅዶላቸው በነበረው የደመወዝ ስኬል እየተጠቀሙ ይቆያሉ፡፡ ሆኖም ይህ የሽግግር ጊዜ የደመወዝ ስኬል በመንግሥት ውሳኔ መሠረት ወደፊት ሲሻሻል የተቋሙ የደመወዝ ስኬል የሚካተት ሆኖ ሲገኝ የተቋሙ የደመወዝ ስኬል እንደሌሎቹ የከተማው አስተዳደር ተቋማት በሀገር አቀፉ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ስኬል ውስጥ የሚካተት ይሆናል፡፡
 ከነባሩ የሥራዎች ምዘና ሥርዓት ወደ ነጥብ የሥራዎች ምዘና ዘዴ የሚደረገውን የደመወዝ ስኬል ሽግግር አፈጻጸም ከዚህ በታች በተመለከተው መሠረት ይሆናል፡፡
 የነባር የሥራ መደብ መጠሪያና ደረጃ በአዲስ መጠሪያና ደረጃ መቀየሩን የሚያረጋገጥ የመሸጋገሪያ ሠንጠረዥ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ጸድቆ ያልደረሰው ተቋም የሠራተኛ ድልድል መፈጸምም ሆነ የደመወዝ ማስተካከያ ማድረግ አይችልም፡፡
 በነጥብ የሥራ ምዘና ዘዴ በተመዘኑ የሥራ መደቦች ላይ የመጀመሪያ ድልድል ከተፈጸመ በኋላ በተካሄደ የአደረጃጀት ለውጥ ወይም ሌላ ምክንያት ዳግም መመዘን ባለበት የሥራ መደብ ላይ የተደለደለ ሠራተኛ ክፍያውን እንዲያገኝ የሚደረገው በቅድሚያ የሥራ መደቡ ምዘና የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ከጸደቀ በኋላ ነው፡፡
o የነጥብ የሥራ ምዘና ዘዴ የመንግስት ሠራተኞች ድልድል አፈጻጸም መመሪያ የሚጠይቀውን መስፈርት ማሟላታቸው ተረጋግጦ ድልድል የጸደቀላቸው ሠራተኞች፡-
ሀ) የመደበኛ የደመወዝ ጭማሪ ኡደት አይለወጥም፣
ለ) ለደረጃ እድገት የአንድ ዓመት መቆያ ጊዜ አይጠበቅበትም፣
o ከነባሩ የሥራዎች ምዘና ዘዴ ወደ ነጥብ የሥራዎች ምዘና የሚደረገውን ሽግግር ተግባራዊ ለማድረግ በተደረገ የሠራተኞች ድልድል ሠራተኛው የያዘው የሥራ መደብ በእንደገና ምደባ ከፍ ብሎ ከተመደበ የሥራ መደቡን የያዘው ሠራተኛ መስፈርቱን እስካሟላ ድረስ የሥራ መደቡ የሚያስገኘውን ደረጃና ደመወዝ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
o ከፍ ባለ የሥራ ደረጃ ላይ በተጠባባቂነት የተመደበ ሠራተኛ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ልዩነት የሚታሰብለት በድልድሉ በተመደበበት ደረጃ ላይ ነው፡፡
o በጥር ወር 2009 ዓ.ም. ተሻሽሎ በሥራ ላይ በዋለው የደመወዝ ስኬል ጣሪያ ላይ የደረሰና በአዲሱ የደመወዝ ስኬል ጣሪያው የሚነሳለት ሠራተኛ በተመደበበት የሥራ ደረጃ የአዲሱን የደመወዝ ስኬል ጣሪያ ሳያልፍ ማስተካከያውን እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
 አንድ ሠራተኛ የሚከፈለው ደመወዝ በደመወዝ ስኬሉ ለተደለደለበት የሥራ መደብ ከተወሰነው የመነሻ ደመወዝ በታች ከሆነ፤ የሠራተኛው ደመወዝ ወደ መነሻ ደመወዝ ከፍ እንዲል ይደረጋል።
 የሠራተኛው ደመወዝ ከመነሻ በላይ ሆኖ፤ በመነሻና በአንደኛው የእርከን ደመወዝ መካከል ወይም በሁለት የእርከን ደመወዞች መካከል ከሆነ በአቅራቢያው ወደ አለው ከፍ ያለ የእርከን ደመወዝ ይስተካከላል።
 የሠራተኛው ደመወዝ ከደመወዝ ስኬሉ የመነሻ፣ የእርከን ወይም የጣሪያ ደመወዝ ጋር ከገጠመ ወይም ከጣሪያ በላይ ከሆነ የያዘውን ደመወዝ እንደያዘ ይቀጥላል።
 ቢሮው በአንድ ተቋም ከተፈጸሙ የሠራተኞች ድልድል መካከል በተለያዩ ሕግን ባልተከተሉ አሠራሮች ምክንያት ያልተቀበለው ካለ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ጭማሪው የሚሰጠው በድልድል አፈጻጸም መመሪያው መሠረት ሠራተኛው በሚያሟላበት ደረጃ ከተደለደለ በኋላ ነው፡፡
o ከፍ ካለ የሥራ ደረጃ ላይ በሚታሰብ ደመወዝ ተቀጥሮ እየተቀነሰ የሚከፈለው ሠራተኛ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ተጠቃሚ የሚሆነው በሚያሟላበት ደረጃ ላይ ተመሥርቶ ይሆናል፡፡
o በሙከራ ቅጥር ላይ የሚገኝ ሠራተኛ የዚህ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
o በዲሲፕሊን ጉድለት ምክንያት ከደረጃው ዝቅ ያለና ደመወዙ የተቀነሰበት ሠራተኛ ማስተካከያው የሚሰጠው በተቀነሰው ደረጃና ደመወዝ ላይ ታስቦ ነው፡፡ ሆኖም በተወሰነ የጊዜ ገደብ ከደረጃና ደመወዝ ዝቅ የተደረገ ሠራተኛ የጊዜ ገደቡ ደርሶ ወደ ቀድሞ ደረጃው ሲመለስ ከተመለሰበት ጊዜ ጀምሮ በአዲሱ የደመወዝ ስኬል ተገቢው ደመወዝ ይሰጠዋል፡፡
ልዩ ፈቃድ ተሰጥቶት በፕሮጀክት የአፈፃፀም መመሪያ መሠረት ወደ ፕሮጀክት የተዛወረ ሠራተኛ፡-
---------------------------------------
ሀ) መደበኛ ደመወዙ በነበረበት መሥሪያ ቤት የሚከፈለው ከሆነ ወደ ፕሮጀክት ከመዛወሩ በፊት የነበረ መደበኛ ደመወዙን መሠረት በማድረግ ለተደለደለበት የሥራ መደብ/ደረጃ/ የተወሰነው አዲሱ ደመወዝ ተጠቃሚ ይሆናል።
ለ) ደመወዙ ከፕሮጀክቱ እየተከፈለው የሚሠራ ከሆነ ወደ መደበኛ ሥራው ሲመለስ ለሚደለደልበት የሥራ መደብ/ደረጃ/ የተወሰነው አዲሱ ደመወዝ ተጠቃሚ ይሆናል።
 ይህ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ጊዜያዊ ወይም የኮንትራት ሠራተኛን አይመለከትም፡፡ ሆኖም በነጥብ የሥራ ምዘና ዘዴ ተመዝኖ ደረጃ በወጣለት ቋሚ የሥራ መደብ ላይ መመሪያውን ተከትሎ የተቀጠረ ጊዜያዊ ወይም የኮንትራት ሠራተኛ የደመወዝ ማስተካከያው ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
 በተለያዩ ምክንያቶች ከመደበኛ ሥራው ተለይቶ የቆየ ሠራተኛ ወደ ሥራው እንዲመለስ ሲደረግ በነጥብ የሥራ ምዘና ዘዴ ተመዝኖ ደረጃ በወጣለት የሥራ መደብ ላይ እንዲመደብ ከተደረገ በኋላ ደመወዙ ወደ አዲሱ የደመወዝ ስኬል እንዲሸጋገር ይደረጋል፡፡
 ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ መመሪያ እስከወጣበት ቀን ድረስ ከሥራ የለቀቀ ሠራተኛ ከሥራ እስከተለየበት ቀን ድረስ ያለው ደመወዙ በአዲሱ የደመወዝ ስኬል መሠረት ተሰልቶ ይከፈለዋል፡፡
 ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2012 ዓ.ም. በሞት የተለየ ሠራተኛ በሞተበት ወር ደመወዙ በአዲሱ የደመወዝ ስኬል መሠረት ተሰልቶ ለወራሾቹ ይከፈላል፡፡
 ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ መመሪያ እስከወጣበት ቀን ድረስ በሞት የተለየ ሠራተኛ ከብር 1000 በላይ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ልዩነት የሚያገኝ በመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2010 አንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የተመደበበት ደረጃ ሙሉ የሶስት ወር ደመወዝ በአንድ ጊዜ ለወራሾቹ ይከፈላል፡፡
 መሥሪያ ቤቱ ባወቀው በማናቸውም ምክንያት በድልድል ወቅት ሥራ ላይ ባለመኖሩ ያልተደለደለ ሠራተኛ ቅድሚያ በሥራ ላይ ባሉ መመሪያዎች መሠረት ወደ ምድብ ሥራው እንዲመለስ ሲደረግ፣ በነጥብ የሥራ ምዘና ዘዴ ተመዝኖ ደረጃ በወጣለት ሥራ መደብ ላይ እንዲመደብ በማድረግ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
 “አንድ ሠራተኛ ለአንድ የሥራ መደብ የተቀመጠውን የሥራ ልምድ ለማሟላት እስከ አንድ ዓመት ከጐደለው እና ለሥራ መደቡ የተቀመጠውን የተፈላጊ ችሎታ የሚያሟላ ሌላ ሠራተኛ ከሌለ ሠራተኛውን ደልድሎ ማሠራት ይቻላል፡፡” በሚለው መሠረት ለተደለደለበት ደረጃ እስከ አንድ ዓመት የሚጎድለው ሠራተኛ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ጭማሪ ተጠቃሚ የሚሆነው የተደለደለበት የሥራ መደብ የሚጠይቀውን ቀሪ የሥራ ልምድ ሲያሟላ ነው፡፡
 በሥራው ልዩ ባህርይ ምክንያት እያስተማረ የህክምና አገልግሎት የሚያበረክት የጤና ባለሙያ የማስተማር ሥራው እንደተጠበቀ ሆኖ እንደሁኔታው በአካዳሚክ ወይም በጤና ሙያ /ከፍ ባለው/ ደረጃ ላይ ተደልድሎ ሊሠራ ይችላል፡፡
 በነባሩ የጤና ባለሙያዎች የእድገት መሰላል በሙያው የመጨረሻ የእድገት ተዋረድ ላይ ደርሰው ከነበሩ ሙያተኞች መካከል በያዙት ሙያ ከ10 ዓመት በላይ አገልግሎት ያለው ወይም ከጀማሪ ስፔሻሊስቶች በስተቀር በቀድሞው ምደባ ፕሣ-6/1 ደረጃ ላይ ደርሶ በሙያው አንድ ዓመትና በላይ በማገልገል ቢያንስ 11 ዓመት የሥራ ልምድ ያለው የጤና ባለሙያ በአዲሱ የሙያው እድገት መሰላል የመጨረሻው ተዋረድ/ተዋረድ IV/ ላይ ተመድቦ በደረጃው 3ኛ እርከን ላይ የተመለከተውን ደመወዝ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
 የከፍተኛ ትምህርት የአካዳሚክ ባለሙያዎች፣ የቴክኒካል ረዳቶች፣ ተመራማሪዎች፣ መደበኛ መምህራን፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አሰልጣኞች፣ ኢንስትራክተሮች እና ሌሎች ለካርየር ዕድገት በተዘጋጁ ልዩ መስፈርቶች ይጠቀሙ በነበሩ ተቋማት ያሉ ሙያተኞቻቸው በነበሩበት ደረጃ ያለውድድር ከተደለደሉ በኋላ ወደ ቀጣዩ የእድገት መሰላል የሚሸጋገሩት ለደረጃው የተቀመጡ ነባር መስፈርቶችን ሲያሟሉ ነው፡፡
 የኮሌጅ የትምህርት ደረጃና በታች የትምህርት ዝግጅት በሚጠይቁ የሥራ መደቦች ላይ የሥራ መደቡ የሚጠይቀው የትምህርት ደረጃ ሳይኖረው በልዩ ሁኔታ ለአንድ ጊዜ እንዲደለደሉ ጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥር ፐሰሚ/30/ጠ10/91/17 በተጻፈ ደብዳቤ ሸኝነት በተላከው ሰርኩላር መሠረት የተደለደለ ሠራተኛ የተመደበበት ደረጃ የሚያስገኘውን የመሸጋገሪያ ደመወዝ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
 ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም ከደረጃ I እስከ ደረጃ V ሠልጥነው የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ሳይኖረው ባለው የትምህርት ምስክር ወረቀት ለአንድ ጊዜ የተደለደለ ሠራተኛ የተመደበበት ደረጃ የሚያስገኝለትን የመሸጋገሪያ ደመወዝ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
 በደመወዝ ስኬል ሽግግር የሚያገኘው የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ መጠን ለሶስት ተካፍሎ የመሸጋገሪያ ደመወዝ እንዲከፈለው የተደረገ ሠራተኛ እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም. ድረስ ከደመወዙ ላይ ታክስ የሚቀነሰው ለበጀት ዓመቱ ከተፈቀደለት የመሸጋገሪያ ደመወዝ ላይ ነው፡፡
 ከ2012 እስከ 2014 የበጀት ዓመቶች ባለው ጊዜ ውስጥ በጡረታ ከሥራ ከሚገለሉ ሠራተኞች መካከል፡-
ሀ) ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በጡረታ ከሥራ የሚለይ ሠራተኛ ወደ አዲሱ የደመወዝ ስኬል ሲሸጋገር ሙሉ የደመወዝ መሸጋገሪያውን እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
ለ) ከሐምሌ1 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በጡረታ ከሥራ የሚለይ ሠራተኛ ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለተመደበበት ደረጃ የተወሰነውን የደመወዝ መሸጋገሪያ በዚህ መመሪያ ከተከፈለው በኋላ የ2013 የበጀት ዓመት ሙሉ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያውን እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
ከላይ የተመለከተው የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ዕድሜው 60 ዓመት ሳይሞላው በፈቃዱ በጡረታ ከሥራ የሚለይ ሠራተኛን አይመለከትም፡፡
የደረጃ ዕድገት የሚያገኙ ሠራተኞችን እና አዲስ ተቀጣሪን በሚመለከት፡-
 የነጥብ የሥራ ምዘና ሥርዓት ከክፍያ ጋር ከተሳሰረ በኋላ በቀጣይ ሙሉ ክፍያውን በሶስት እኩል መጠን እንዲከፈለው የተደረገ ሠራተኛ በያዘው ደረጃ ላይ ሌላ ሠራተኛ በደረጃ ዕድገት ወይም በቅጥር በአዲሱ የደመወዝ ስኬል ላይ ሲመደብ፣ የደመወዝ ስኬሉ ማስተካከያው ደረጃ በደረጃ እንዲከፈላቸው ከተደረጉ ሌሎች ነባር ሠራተኞች የክፍያ መጠን መብለጥ ስለሌለበት፡-
o የደረጃ ዕድገት የሚያገኙ ሠራተኞችን በሚመለከት፡-
-------------------------------------
• ይህ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ አፈጻጸም መመሪያ ከጸደቀበት ወር ቀጥሎ እስከ ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ድረስ የደረጃ ዕድገት ካገኙ ሠራተኞች መካከል በደረጃ ዕድገት ስም ያገኘው የገንዘብ መጠን፡-
• ሀ) እስከ ብር 1000 ከሆነ ሠራተኛው የደመወዝ ልዩነቱን የደረጃ ዕድገት ካገኘበት ወር መጀመሪያ ቀን ጀምሮ ይከፈለዋል፡፡
• ለ) ከብር 1000 በላይ ሆኖ በ2012 ዓ.ም. የበጀት ዓመት የደረጃ ዕድገት ካገኘ የደረጃ ዕድገት የደመወዝ ልዩነቱን ለሶስት በማካፈል ወጤቱን እየተከፈለው ባለው የወር ደመወዝ ላይ፡-
• ካደገበት ወር እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም. ድረስ 1/3ኛ፣
• ከሀምሌ ወር 2012 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም. ሁለተኛውን 1/3 እና
• ከሀምሌ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የመጨረሻውን 1/3ኛ፣
 የደመወዝ ማስተካከያ በመጨመር የሠራተኛው ደመወዝ እንደሁኔታው ወደ ተመደበበት ደረጃ የመነሻ ወይም የእርከን ደመወዝ ላይ እንዲያርፍ ይደረጋል፡፡
 ከብር 1000 በላይ ሆኖ በ2013 ዓ.ም. የበጀት ዓመት የደረጃ ዕድገት ካገኘ የደረጃ ዕድገት የደመወዝ ልዩነቱን ለሁለት በማካፈል ወጤቱን እየተከፈለው ባለው የወር ደመወዝ ላይ፡-
• ካደገበት ወር እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም. ድረስ ½ኛ የደረጃ እድገት ልዩነቱን በመጨመር እና
• ከሀምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የመጨረሻውን ½ኛ የደረጃ ዕድገት ልዩነቱን በመጨመር፣
 የሠራተኛው ደመወዝ ወደ ተመደበበት ደረጃ የመነሻ ወይም የእርከን ደመወዝ ላይ እንዲያርፍ ይደረጋል፡፡
 ከሀምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የደረጃ ዕድገት የሚያገኝ ሠራተኛ ለሚያድግበት ደረጃ የተወሰነውን የመነሻ ወይም የእርከን ደመወዝ ካደገበት ወር መጀመሪያ ቀን ጀምሮ ይከፈለዋል፡፡
አዲስ ተቀጣሪን በሚመለከት፡-
------------------------------
ይህ መመሪያ ከፀደቀበት ቀን ማግስት ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ፡-
ሀ) ከደረጃ I እስከ ደረጃ VII ባሉ ደረጃዎች የተቀጠረ ሠራተኛ የተቀጠረበትን ደረጃ የመነሻ ደመወዝ እንዲያገኝ ይደረጋል፣
ለ) ከደረጃ VII በላይ ባሉ ደረጃዎች የሚቀጠር ሠራተኛ በተቀጠረበት የሥራ ደረጃና ከተቀጠረበት ደረጃ በአንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ በሚገኝ ደረጃ መካከል ያሉ ሶስት የእርከን ልዩነቶችን በየበጀት ዓመቱ ዝቅ ባለው ደረጃ የመነሻ ደመወዝ ላይ አንድ አንድ እርከን በመጨመር የወር ደመወዝ እንዲከፈለው በማድረግ ከሀምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀጠረበትን ደረጃ የመነሻ ደመወዝ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡›
ምሳሌ 1 የደረጃ XV መነሻ ደመወዝ ብር 10150፣ የደረጃ XIV መነሻ ደመወዝ ደግሞ ብር 9056 ቢሆን፣ እንዲሁም የዚሁ ደረጃ 1ኛ እርከን ደመወዝ ብር 9420፣ የደረጃው የ2ኛ እርከን ደመወዝ ብር 9785 እና የ3ኛው እርከን ደመወዝ ብር 10150 ቢሆን አዲሱ የደመወዝ ስኬል ተግባራዊ ከሆነበት ቀን ማግስት ጀምሮ በደረጃ XV የተቀጠረ ሠራተኛ የተቀጠረበት ደረጃ እንደተጠበቀ ሆኖ፡-
እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም. ድረስ ከተቀጠረበት ደረጃ አንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ በሚገኘው የደረጃ XIV መነሻ ደመወዝ /ብር 9056/ ላይ አንድ እርከን በመጨመር የደረጃው 1ኛ እርከን ደመወዝ የሆነውን ብር 9420፣
በሁለተኛው የበጀት ዓመት /ከሀምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም. /የደረጃ XIV 2ኛ እርከን ደመወዝ የሆነውን ብር 9785/፣
በሶስተኛው የበጀት ዓመት /ከሀምሌ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀጠረበት ደረጃ XV የመነሻ ደረጃ የመነሻ ደመወዝ የሆነውን ብር 10150፣እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
ሐ) ከሀምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የሚቀጠር ሠራተኛ ከተቀጠረበት ደረጃ በአንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ የሚገኝ የሶስት እርከን የገንዘብ መጠንን ለሁለት በማካፈል ከተቀጠረበት ደረጃ በአንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ በሚገኝ የመነሻ ደመወዝ ላይ በመደመር የመጀመሪያው ዙር ደመወዙ በየወሩ የሚከፈለው ሲሆን፣ ከሀምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የቀረውን ገንዘብ በሚከፈለው ደመወዝ ላይ በመጨመር የተቀጠረበትን ደረጃ የመነሻ ደመወዝ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
ምሳሌ 2 ከላይ በምሳሌ አንድ ላይ በተጠቀሰው ደረጃ XV ላይ በ2013 ዓ.ም. የበጀት ዓመት /ከሀምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2ዐ13 ዓ.ም. /የተቀጠረ ሠራተኛ የተቀጠረበት ደረጃ እንደተጠበቀ ሆኖ ከተቀጠረበት ደረጃ በአንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ በሚገኘው የደረጃ XIV መነሻ ደመወዝን ከደረጃው የ3ኛ እርከን በመቀነስና ልዩነቱን ለሁለት በማካፈል /10150- 9056 = ብር 1094/ ስለሚሆን ብር 1094ን ለሁለት በማካፈል /1094/2/ የተገኘውን ብር 547 ደረጃ XIV መነሻ ደመወዝ በሆነው ብር 9056 ላይ በመደመር ብር /9056 + 547/ ብር 9603 እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም. ድረስ እንዲከፈለው ይደረጋል፡፡
ከሀምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ብር 9603 ላይ ቀሪውን 547 በመጨመር /9603 + 547 = ብር10150/ የሠራተኛው ደመወዝ የተቀጠረበት ደረጃ XV መነሻ ደመወዝ በሆነው ብር 10150 ላይ እንዲያርፍ ይደረጋል፡፡
መ) ከሀምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የሚቀጠር ሠራተኛ የተቀጠረበትን ደረጃ የመነሻ ደመወዝ ከተቀጠረበት እለት ጀምሮ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
ከዚህ መመሪያ ጋር የሚቃረን ማንኛውም መመሪያ በዚህ መመሪያ ውስጥ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ
መስከረም 2012 ዓ.ም

Comments

  1. Odterochin endet aytachihu new lmn bebord qyhonim ere endelifatachin bebord yitedader

    ReplyDelete
  2. ጤና ይስጥልኝ በምህዲስና የተቀጠርነዉ በየወረዳዉ እኩል ክፍያ አይደለም የሚሰማን ሰዉም አጣን ከተቀጠርን ከሁለት አመት በላይ የሆነን እስካሁን 4551 ነዉ የሚከፈለን አልተስተካከለነም ሰሃላ ሰየምት ወረዳ ዋግኸምራ ዞን

    ReplyDelete
  3. ዩንቨርሲቲ ክሊኒክ ላይ መች ተሰርቷልና ገቢወች የምትሉት

    ReplyDelete

Post a Comment

Popular posts from this blog

የነጥብ ስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት

አዋጅ ቁጥር 1064/2010