“ንፁህ እጆችና መፀዳጃ ቤት ለሁሉም”

ዓለም አቀፍ እጅ የመታጠብና መፀዳጃ ቤት ቀን “ንፁህ እጆችና መፀዳጃ ቤት ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል በየካ ክፍለ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡

የካ ማህበራዊ ሚዲያ (ሕዳር 10/2012 ዓ.ም)


የየካ ክፍለ ከተማ ጤና ፅ/ቤት ዓለም አቀፍ እጅ የመታጠብና መፀዳጃ ቤት ቀንን በትምህርት ቤቶች ተገቢንት ያለው የእጅ አስተጣጠብ ስርዓትን በማስተማር እየተከበረ ይገኛል፡፡  የዘንድሮው የእጅ መታጠብ ቀን “ንፁህ እጆችና መፀዳጃ ቤት ለሁሉም!” በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ ይውላል፡፡ለመሆኑ እጅ መታጠብ ለምን ያስፈልጋል? እጅ የመታጠቢያ ወሳኝ ጊዜያት የትኞቹ ናቸው? እጃችን ስንታጠብስ ትኩረታችን ምን ላይ ይሁን? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ይዘንላችሁ ቀርበናል ተከታተሉን፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ መከታተያ ቻናሎቻችን ከፌስቡክ በተጨማሪ፡

1.       እጅ መታጠብ ለምን ያስፈልጋል

-----------------------------
የተለያ ተግባራትን በምንሰራበት ወቅት እጃችን የተለያዩ ቆሻሻዎችንና በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን ሊነካ ይችላል፡፡ እነዚህ ተህዋስያን ጥቃቅን በሆኑ የእጆቻችን መተጣጠፊያ ቦታዎች መደበቅና መራባት ስለሚችሉ ለተለያዩ በሽታዎች ይዳርጉናል፡፡ በትክክል እጅን መታጠብ ማለት የጤና ጠንቅ ከሆኑ ተህዋስያን ጋር የሚደረግ የ20 ሰከንድ ትግል ማለት ነው፡፡ ይህ ተግባር ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ሰዎች በቀላሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚተገብሩት ፍቱን መድሐኒት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡

2.       እጅ የመታጠቢያ ወሳኝ ጊዜያት
---------------------------

እጆቻችንን በተደጋጋሚ መታጠብ ቢያስፈልግም በደንብ ትኩረት ልንሰጥባቸው የሚገቡ ጊዜያት ከመፀዳጃ ቤት መልስ ፣ ማንኛውንም ምግብ ከማዘጋጀት በፊት ፣ ምግብ ከመመገብ በፊት ፣ ህፃናትን ካፀዳዱ በኋላ ፣ ህፃናትን ጡት ከማጥባትና ከመመገብ በፊት እና ማንኛውንም ቆሻሻ ካፀዱ በኋላ ናቸው፡፡

3.       እጆቻችንን ስንታጠብ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች
----------------------------------------

·         ጥፍሮቻችን ሁልጊዜ በአጭሩ ሊቆረጡና ሊስተካከሉ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ በዓይናችን ልናያቸው የማንችላቸው በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ በሽታ አምጪ ተህዋስያን እንደ ባክቴሪያ ፣ ፈንገስ ፣ አሜባ ፣ ጃርዲያ ፣ የወስፋትና የኮሶ ትል እንቁላሎች ፣ መደበቂያና መራቢያ ቦታ ስለሚሆን ሊፀዳ ይገባል፡፡
·         በየጣቶቻችን መካከል የሚገኙ ቦታዎች ፣ መገጣጠሚያዎችና መተጣጠፊያዎች በሽታ አምጨ ተህዋስያንን ሊደብቁና ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ እጅ በመታጠብ ጊዜ ትኩረት ሰጥተን በቂ ውሐና ሳሙና በመጠቀም ልናፀዳቸው ይገባል፡፡

4.       የመፀዳጃ ቤት አስፈላጊነት
-------------------------------

በሐገራችን ደረጃውን የጠበቀና ንፁህ የመፀዳጃ ቤት ተጠቃሚ ቁጥር ከአጠቃላይ ህዝባችን ከግማሽ በታች ነው፡፡ በመፀዳጃ ቤትና የግል ንፅህና እጦት ምክንያት የሚመጡ ተቅማጥና መሰል የጤና ችግሮች በርካታ ሰዎችን በተለይ ህፃናትን ለህመምና ሞት ይዳርጋሉ ፤ ከትምህርት ገበታ ያስቀራሉ ፤ ቤተሰብንም ላልታሰበ የህክምና ወጪ ይዳርጋሉ፡፡ ሰዎችን ምርታማነት በማዳከም በቤተሰብና የሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ መፀዳጃ ቤቶች እነዚህን ሁሉ የጤናና የኢኮኖሚ ችግሮች ያስቀራሉ፡፡ ይህ የመፀዳጃ ቤት ቀን ሲከበር መፀዳጃ ቤቶችን ማግኘት መብት በመሆኑ መንግስት ሰዎች ክብራቸውን የሚመጥን መፀዳጃ እንዲያገኙ እንዲሰራ ጥሪ በማስተላለፍ ነው፡፡

“እጅን በውሐና በሳሙና አዘውትሮ መታጠብ ተቅማጥንና ይህን ተከትለው የሚመጡ የህጻናት ጤና ችግሮችን 30 በመቶ ይቀንሳል፡፡


ምንጭ ፡ የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት

Comments

Popular posts from this blog

የደመወዝ ስኬል አፈጻጸም መመሪያ

በዜሮ ዓመት የወጣ ክፍት የስራ ማስታወቂያ

የነጥብ ስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት