የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣ ረቂቅ አዋጅ

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣ ረቂቅ አዋጅ

------------------------------

መግቢያ


ሰብዓዊ ክብርን የሚገረስሱ እና ሆን ተብሎ የሚሰራጩ ሃሰተኛ ንግግሮችን በሕግ መከልከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኝቱ፤ የጥላቻ ንግግርና የሃስተኛ መረጃ ስርጭት የሚያስከትሉት ግጭትና ጉዳት ለእኩልነት፣ለሰላም፣ ለዲሞክራሲና ለሕዝቦች አንድነት ትልቅ ጠንቅ በመሆኑ፤ መሰረታዊ መብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች በሕግ የተደነገጉ፣ በዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውን አላማ ለማስፈጸም የሚወጡና ተመጣጣኝ መሆን እንዳለባቸው በመገንዘብ፤ በኢትዮጲያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት እንቀፅ 55(1) መሰረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ አጠቃላይ
1. አጭር ርዕስ


ይህ አዋጅየጥላቻ ንግግርንና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣ አዋጅ ቁጥር .../2012“ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2. ትርጉም

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካለሆነ በቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፡-

1. “ንግግርማለት በቃል፣ በጽሑፍ፣ በምሥልና ሥዕል፣ በቅርጻ ቅርጽ እና በሌሎች ተመሳሳይ መንገዶች መልእክትን የማስተላለፍ ተግባር ነዉ፡፡

2. “የጥላቻ ንግግርማለት የሌላን ግለሰብን፤ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማህበረሰብን ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ቀለምን፤ ጾታን፤ አካል ጉዳተኝነትን፤ ዜግነትን፤ ስደተኝነትን፤ ቋንቋን፤ ዉጪያዊ ገጽታን፤ መሰረት በማድረግ ፣ሆነ ብሎ እኩይ አድርጎ የሚስል፤ የሚያንኳስስ፤ የሚያስፈራራ፤ መድልዎ እንዲፈጸም፤ ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ንግግር ነው።

3. “ሃስተኛ መረጃማለት የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት የሆነና ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ግልጽ በሆነ መልኩ ክፍ ያለ ንግግር ነው።

4. "ብሮድካስት ማድረግማለት በሬዲዮ ወይም በቴሌቪዥን ሥርጭት ማድረግ ነዉ፡፡

5. "ማህበራዊ ሚዲያ" ማለት ሰዎች መልዕክት ለመለዋወጥ ትስስር ለማዳበር፤ ሀሳብ ለመጋራት የሚጠቀሙበት በኢንተርኔት አማካኝነት በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ለሆኑ ሰዎች መረጃ የሚደርስበት መንገድ ነዉ፡፡
6. "ጥቃት" ማለት በግለሰብ፤ ቡድን ወይም ማህበረሰብ ላይ የሚደርስ የህይወት፤የአካል፤ የስነ -ልቦና ወይም ቁሳዊ ጉዳት ነው።
7. "ሰዉ" ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ ሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው። 
8. ማንኛዉም በወንድ ጾታ የተገለጸ ለሴት ጾታ ያገለግላል፡፡

3. አላማ
የአዋጁ አላማዎች፤


  • ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብዓዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደህነነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር ኢንዲቆጠቡ ማስቻል፤
  • በማህበረሰቡ ውስጥ እኩልነት እንዲሰፍን፣ መከባበር እንዲኖርና መግባባትና ዲሞክራሲያዊ ስርዐት እንዲጎለብት ማድረግ፤
  • ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት አደጋ የሆኑ የጥላቻ አመለካከትና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን መስፋፋትን እና ተያያዥ ወንጀሎችን መከላከል እና መቀነስ ናቸው።

ክፍል ሁለት 
የተከለከሉ ተግባራት

4. የጥላቻ ንግግር


1. ሆነ ብሎ የሌላን ግለሰብን፤ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማህበረሰብን ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ቀለምን፤ ጾታን፤ አካል ጉዳተኝነትን፤ ዜግነትን፤ ስደተኝነትን፤ ቋንቋን፤ ዉጪያዊ ገጽታን፤ መሰረት በማድረግ እኩይ አድርጎ የሚስል፤ የሚያንኳስስ፤ የሚያስፈራራ፤ መድልዎ እንዲፈጸም፤ ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ጥላቻ አዘል -

. መልእክቶችን በመናገር፤
. ፅሁፍ በመፃፍ፤
. የኪነጥበብ እና እደ ጥበብ ውጤት በመስራት፤
. ፅሁፍ፤ ምስል፤ ስእል፤ የኪነጥበብ እና እደ ጥበብ ውጤት፤ የድምጽ ቅጂ ወይም ቪድዮ በማተም፤ በማሳተም ወይም በማሰራጨት፤
. መልእክቶችን ብሮድካስት ማድረግ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨት፤ ወይም . በሌሎች ማናቸዉም መገናኛ መንገዶች ለህዝብ መልእክቱ እንዲደርስ ማድረግ ክልክል ነው፡፡

2. ማንም ሰው በዚህ አንቀጽ ንኡስ ቁጥር 1 ላይ በተገለጸዉ አግባብ ጥላቻ የሚያስተላልፍ መልእክት ለማሕበረሰቡ ወይም ለሶስተኛ ወገን እንዲደርስ በማሰብ በህትመት ወይም በፅሁፍ መልክ ይዞ መገኘት የተከለከለ ነው፡፡

5. የሃሰት መረጃ


የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው፣ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ግልጽ በሆነ መልኩ ክፍ ያለ መረጃን ሆነ ብሎ በማንኛውም መንገድ ማሰራጨትና ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ የተከለከለ ነው።

6. ልዩ ሁኔታ


1. የዚህ አዋጅ አንቀፅ 4 እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር ተወስዶ በወንጀል የማያስጠይቀው፡ 

. ድርጊቱ ለትምህርታዊ ወይም ሳይንሳዊ ምርምር የተደረገ እንደሆነ፤

. የሚዛናዊ እና ትክክለኛ ዘገባ፤ በዲሞክራሲያዊ ስርዐት ውስጥ ተቀባይነት ያለው ትችትና የፖለቲካ ንግግር፤ የማስታወቂያ ወይም ማስጠንቀቂያ አካል እንደሆነ፤

. በቅን ልቦና የሚደረጉ ሃይማኖታዊ አስተምሮት ወይም አተረጓጎም ከሆነ ነዉ፤

2. የዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ንግግር እንደ ሃሰተኛ መረጃ ተወስዶ በወንጀል የማያስጠይቀው፣

. ንግግሩ የጥሬ ሃቅ ዘገባ ወይም ዜና ከመሆን ይልቅ ወደ ፖለቲካ አስተያየትና ትችትነት ያጋደለ ከሆነ፣
. ንግግሩ ቀልድ፣ ስላቅ ወይም ልብወለድ መሆኑ ግልጽ ከሆነ፣
. ንግግሩን ያደረገው ሰው የመረጃውን እውነተኛነት ለማረጋገጥ በሱ ሁኔታ ካለ ሰው የሚጠበቀውን ምክንያታዊ ጥረት ያደረገ እንደሆነ ነው።

ክፍል ሶስት የወንጀል ተጠያቂነት


7 . የወንጀል ተጠያቂነት


1. ማንም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀፅ 4(1) (-) የተመለከቱቱትን የተከለከሉ ተግባራት የፈጸመ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ እስከ ሶስት አመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም እስከ ብር 10,000 በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

2. በዚህ አዋጅ አንቀፅ 4 ንዑስ አንቀፅ 1 የተከለከሉት ተግባራት በመፈጸማቸው የተነሳ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም የተሞከረ ከሆነ የተከለከሉትን ተግባራት የፈጸመዉ ሰው እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አምስት አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።

3. ማንም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀፅ 4(2) ላይ የተመለከተውን የተከለከለ ተግባር የፈጸመ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከብር 5000 ያልበለጠ መቀጮ ይቀጣል፡፡

4. ማንም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 የተመለከትውን የተከለከለ ተግባር ከፈጸመ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አንድ አመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም እስከ ብር 3,000 በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

5. በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 የተመለከተውን የተከለከለ ተግባር የፈጸመው ሰው ድርጊቱን የፈጸመው ከአምስት በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚድያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ሶስት አመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም እስከ ብር 10,000 በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል::

6. በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 የተከለከለው ተግባር በመፈጸሙ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም የተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ውይም ግጭት የተከሰተ እንደሆነ የተከለውን ተግባር የፈጸመዉ ሰው እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አምስት አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።

7. በዚህ አዋጅ የወንጀል ተጠያቂ የሆነ ሰውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ሲያምንና የተከለከለው ተግባር በመፈጸሙ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ያልተፈጸመ ወይም ያልተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ውይም ግጭት ያልተከሰተ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ በእስራት ምትክ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራን በአማራጭ ቅጣትነት ሊወስን ይችላል።

8 . የተቋማትና የአገልግሎት ሰጪዎች ሀላፊነት


1. ማንኛውም የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት በአንቀጽ 5(1) (-) በአንቀጽ 6 የተከለከሉት ንግግሮች እንዳይተላለፉ ወይም እንዳይሰራጩ የመቆጣጠርና የመግታት፣ የተከለከሉ ንግግሮችን በተመለከተ ጠቆማ ሲደርሰውና ጥቆማው አሳማኝ ሲሆን ንግግሩን በአፋጣኝ የማስወገድ ውየም ከስርጭት የማስወጣት ግዴታ አለበት።

2. ማንኛውም የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት በአንቀጽ 9(1) የተንደነገገውን ግዴታውን ለመወጣት የሚያስችለው አሰራርና ፖሊሲ ሊኖረው ይገባል።

3. የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በዚህ አንቀጽ የተቀመጠውን ግዴታቸውን ባግባቡ እንዲወጡ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል።

4. የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን የሃሰት መረጃ ስርጭትና ጉዳትን ለመከላከል የሚረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብሮችንና በማዘጋጀት ተግባራዊ ያደርጋል።

5. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የሚረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብሮችንና በማዘጋጀት ተግባራዊ ያደርጋል።

6. የተቋማትና የአገልግሎት ሰጪዎች ሀላፊነትን ዝርዝር የሚደነግግ ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊወጣ ይችላል።

9. ስለተሻሩ ህጎች


የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ የወንጀል ህግ አንቀጽ 486 በዚህ አዋጅ ተሽሮዋል።

10. አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ

ይህ አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ግዜ ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡


Comments

Popular posts from this blog

የደመወዝ ስኬል አፈጻጸም መመሪያ

በዜሮ ዓመት የወጣ ክፍት የስራ ማስታወቂያ

የነጥብ ስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት