ሰንደቅ አላማ = የሐገራዊ አንድነት ምልክት
ሰንደቅ አላማ = የሐገራዊ አንድነት ምልክት
============================
ሰንደቅ አላማ የሚለው መጠሪያ ከሁለት ቃላት የተገኘ ነው፡፡ ይህም “ሰንደቅ” እና ”አላማ” ከሚሉ ቃላት የተመሰረተ ሲሆን የቃላቱ የተናጥል ትርጉም፡
- ሰንደቅ፡- ማለት ምርኩዝ፣ ምሰሶ፣ በትር ማለት ሲሆን
- ዓላማ፡- ማለት ምልክት፣ አቋም፣ ስብስብ እንዲሁም የነፃነት፣ የሉዓላዊነት ምልክት ማለት ነው፡፡
የሁለቱ ቃላት ጥምረት “ሰንደቅ ዓላማ” የሚለው ቃል በአንድ ላይ የአገር መታወቂያ፣ የሕዝብ አንድነት መጠበቂያ እንዲሁም የክብር መለያ ምልክት የሚለውን ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ህዝብንና መንግስት ሉዐላዊነት፣ ስልጣንና ነፃነት ምልክት ወይም ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
ሰንደቅ አላማ የአገር እና የህዝብ ምልክት ነው፡፡ ሰንደቅ አላማ የሃገር ምልክት በመሆኑ ከሰንደቅ ዓላማው ፊት በቆመ ቁጥር የሃገሩ ምስል የማይከሰትበት ዜጋ የለም፡፡ ከአለም ታሪክ እንደምንረዳው ሃገራትና ዜጎች ከቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ሲላቀቁ መጀመሪያ ከፍ አድርገው የሚያሳዩት ሰንደቅ አላማቸውን ነው፡፡
ህዝቦችና አገራት በሰላም አደባባይም ሆነ በጦር ሜዳ ዉሎ ለድል ሲበቁ ቅድሚያ የሚሰቅሉት ሰንደቅ አላማቸውን ነው፡፡
ይህን በማድረግም ፍቅርና ክብራቸውን እጅግ ከፍ ባለ መልኩ ለሰንደቅ አላማቸው ይገልፃሉ፡፡ ይህ ማለት ህዝቦች በአንድ ሰንደቅ አላማ ስር በመሰባሰብ ሉዓላዊነታቸውን ይገልፃሉ፡፡
ሰንደቃችን ጥቁሮችን ነጻ ያወጣች ፡ የድላችን አርማ ነች። ብዙዎች ደም አፍስሰው አጥንት ከስክሰው ሐገር አቁመውባታል፡፡ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ልምላሜያችንን ተስፋችንንና ድል አድራጊነታችንን የምንገልጽበት አርማችን ነው። ያለ ሰንደቅ ኩራት ፡ ያለምልክት በራስ መቆም ፡ ያለአንድነት ድል የለም። በሰንደቃችን አንድ እንሁን! በአላማ እንተባበር!
(የካ ማህበራዊ ሚዲያ)
ሰንደቃችን ከፍ ይበል !
ሐገራችን ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
Comments
Post a Comment