የኦዳ ወግ

+++ ኦዳ ቡልቱምበሀረርጌ (Odaa Bultum in Hararghe)+++

  • አምስቱ ኦዳዎችና ታሪካዊ አንድምታ

  በጥንት ዘመናት የኦሮሞ ህዝብ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ብሂል ነበረው። ይህም ዲሞክራሲያዊውን የገዳ ስርዓትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ በልዩ ልዩ ምሁራን በተጠናቀሩ ጽሑፎች ተጠቅሷል። ሀገሩን የሚመራው መንግሥት የሚቋቋመውምጨፌ ገዳበተሰኘው ህዝባዊ ሸንጎ በሚመረጡት የመስተዳድር አባላት ነው። ይህ ሸንጎ ጉባኤውን የሚያካሄደው በየስምንት ዓመቱ ነው። ጉባኤው የሚካሄድበት ስፍራም በህግ የተወሰነ ነው። በዚህ ስፍራ ላይ መገኘት ካለባቸው ቋሚ ነገሮች መካከል የላቀ ስፍራ የሚሰጠው ደግሞኦዳየተሰኘው ዛፍ ነው።

 “ኦዳበኦሮምኛየሾላ ዛፍማለት ነው። የገዳ ሸንጎ ጉባኤውን የሚያካሄደው በዚህ ዛፍ ጥላ ስር ነው።ኦዳለጉባኤ ማካሄጃነት የተመረጠው በግርማ ሞገሱና በጥላው ስፋት ብቻ አይደለም። የኦሮሞ ሽማግሌዎች እንደሚናገሩትኦዳ ከሌሎች ዛፎች ይበልጥ ተመራጭ ያደረገው ከክረምት እስከ በጋ ሳይደርቅ (ቅጠሉን ሳያራግፍ) መቆየት የሚችልና የህዝቡን ተስፋና የሀገሩን ልምላሜ የሚጠቁም ምልክት በመሆኑም ጭምር ነው። ታዲያ ሸንጎው በስምንት ዓመት አንዴ የሚሰበሰብ ቢሆንምኦዳ ምን ጊዜም ቢሆን ተፈላጊ ነው። ምንጊዜም ቢሆን ዛፉ የኦሮሞ ህዝብ ልብና የአንድነት ምልክት ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። ስለዚህ የህዝብ ጥበቃና እንክብካቤ ይደረግለታል። እረኞች ፍሬውን ከመብላት ውጪ ሌላ ጉዳት እንዲያደርሱበት አይፈቀድላቸውም። ዛፍ ቆራጮችምኦዳ እንደሌላው ዛፍ መገንደስና የቤት መስሪያ ማድረግ አይችሉም።
***********************************************************
ከአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በፊት በነበረው ጊዜ በሁሉም ክፍላተ ሀገር የሚኖረው የኦሮሞ ህዝብ በአንድ ማዕከል ስር ይተዳደር ነበር። ይህም ማዕከል በዛሬው የባሌ ክፍለ ሀገር፣ ደሎ አውራጃ ውስጥ ባለችውመዳ ወላቡየተሰኘች ቀበሌ ይገኝ ነበር። እያደር የህዝቡ ብዛት ሲጨምርና በርካታ አስተዳደራዊ ችግሮች ሲፈጠሩ ከዋናው ማዕከል በተጨማሪ በየቀጣናው አንዳንድ የገዳ ማዕከል ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። በዚህም መሰረትኦዳ ወላቡ” (ለደቡብ ኦሮሚያ የሚያገለግል)ኦዳ ሮባ” (ለደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ የሚያገለግል)ኦዳ ነቤ” (ለማዕከላዊና ሰሜን ኦሮሚያ የሚያገለግል)ኦዳ ቢሲል” (ለምዕራብ ኦሮሚያ የሚያገለግል) እናኦዳ ቡልቱም” (ለምስራቅ ኦሮሚያ የሚያገለግል) የተባሉ ማዕከላት ተመሰረቱ።ኦዳ ወላቡከደቡብ ቀጣና ማዕከልነቱ በተጨማሪ የህዝቡ ትውፊታዊ የአንድነተ ምልክት እንዲሆንም ተወሰነ። ህዝቡም በየዓመቱ በተመራጮቹ አማካኝነት የታማኝነት ቃሉን በወላቡ ለሚቀመጠውናአባ ሙዳለሚባለው መፈንሳዊ አባት እንዲገልጽ ታወጀ።
****************************************************************
እንግዲህ የዚህ ወግ የትኩረት ነጥብ የሆነውና በምስራቅ ኦሮሚያ የሚገኘው ኦዳ ቡልቱምህልውና የተበሰረው በዚህ መንገድ ነው። በዚህ የገዳ ማዕከል ሲካሄድ የነበረውን የገዳ ባህልና ልማድ የቻልኩትን ያህል አወጋችኋለሁ።

  • የኦዳ ቡልቱም ጉባኤ

የምስራቅ ኦሮሚያ የገዳ ማዕከል በሆነው የኦዳ ቡልቱም ትውፊት የሚተዳደሩት ሶስቱ የሀረርጌ ኦሮሞ ነገዶች (ኢቱ፣ አፍረን ቀሎ እና አኒያ) ናቸው።ኦዳ ቡልቱምየተሰኘው ማዕከል የሚገኘው በአሁኑ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ከበዴሳ ከተማ 20 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ነው። በዚህ የገዳ ማዕከል ከፍተኛ የስልጣን አካል የነበረውጨፌ ገዳየሚባለው የኦዳ ቡልቱም ሸንጎ ነው።

የኦዳ ቡልቱም ሸንጎ ጉባኤውን የሚያካሄድበት ቦታሆረ ባዱይባላል። ቃል በቃልየአሬራ ሐይቅማለት ነው። ስያሜው ለምን እንደወጣለት በትክክል ለማረጋገጥ ባይቻልምጉባኤው በሚካሄድበት ጊዜ ለጉባኤተኞቹ የሚቀርበውን የማሽላ ቂጣና የአሬራ ግብዣ ለመዘከር ነውየሚል መረጃ አለ::

  በዚህሆራ ባዱበተሰኘ ስፍራ ላይ አንድ አነስተኛ ሐይቅ አለ። ይህ ሐይቅ የከብቶች ውሃ ማጠጫ ወይምሆራነው። ከሐይቁ ወዲህ እጅግ የለመለመ የጨፌ መስክ ይታያል። ከጨፌው ወዲህም ሰፊ መስክ አለ። በመስኩ ላይ ያለው ሳር አይታጨድም። ከብቶች ግን እየገቡ ይግጡታል። የመስኩም ሆነ የሀይቁ ይዞታ የጋራ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ከብቱን ወደዚህ ስፍራ እያስገባ ማብላት ይችላል። ከሩቅ ወረዳዎችና አውራጃዎች እንኳ ከብቶቻቸውን እያመጡ በስፍራው የሚያግዱ ሰዎች አሉ። በተለይ በበጋ ወራት በርካታ ህዝብ ከብቶችን ለግጦሽ የሚያሰማራው ወደሆራ ባዱነው።

   የኦዳ ቡልቱም ጉባኤ በሆራ ባዱ የሚካሄደው በየስምንት ዓመቱ ነው። ሸንጎው የሚሰየምበት ቦታም እላይ ከተገለጸው ለምለም መስክ ፈንጠር ብሎ የሚገኝ ገላጣ ስፍራ ነው። በገላጣው ስፍራ መሀል ላይም በተጸውኦ ስሙኦዳ ቡልቱምየሚባለው የኦዳ ዛፍ አለ።ኦዳ ቡልቱምየሚለው ስያሜ ከምን እንደመነጨ የሚነገረው አፈ-ታሪክ ከቦታ ቦታ ይለያያል። አንዳንዶችቡልቱም የሚባል ሰው የመጀመሪያው አባ ገዳ ሆኖ ስለተመረጠ ነውይላሉ። በርካቶች እንደሚሉት ግን የህዝቡ መተዳደሪያና የወደፊት ብሩህ ተስፋ መንገድ ተደርጎ የሚቆጠረው የኦሮሞ ህዝብ ጥንታዊ ህገ-ደንብ የተደነገገበት ስፍራ መሆኑን ለማመልከት ሲባል ነውኦዳ ቡልቱም” (የማደሪያችን ኦዳ) የሚል መጠሪያ ያገኘው።

 የገዳ ጉባኤ በኦዳው ስር በሚካሄድበት ወቅት ጉባኤተኞቹ የሚቀመጡት ከጨፌው እየታጨደ በሚነጠፈው ቄጠማ ላይ ነው። እነዚህ ጉባኤተኞች ሌሊቱን የሚያሳልፉባቸው ስምንት ጎጆዎችም ከጨፌው ይሰራሉ። በየቀኑም ለምግባቸው የሚሆን በሬ ይታረድላቸዋል(ጉባኤው የሚካሄደው ለስምንት ቀናት ነው። ጎጆዎቹም ስምንት ናቸው። አንዳንድ ሰዎች ይህንን ቁጥር ከእድል ጋር ያይዙታል። ይሁንና ስምንት ቁጥር ስምንቱን የገዳ ዓመታት ከመወከሉ ውጪ ከቁጥሩ ጋር የሚገናኝ አንዳች ድብቅ እምነት የለም::
*************************************************************************
      በኦዳ ቡልቱም የሚካሄደው ጉባኤኮረ ገዳወይንምያኢ ገዳይባላል። ከላይ እንደተገለፀው ጉባኤውን የሚያካሄደው ሸንጎጨፌ ገዳተብሎ ይጠራል። የጉባኤው ተሳታፊዎች የሚመረጡት በጎሳና በንዑስ ጎሳ ደረጃ በሚቋቋመው መለስተኛ ሸንጎ አማካኝነት ነው። በነዚህ አነስተኛ ሸንጎዎች የሚመረጥ ሰውሉባተብሎ ይጠራል። ለሉባ ምርጫ በእጩነት የሚቀርብ ሰው እድሜው 40 እና 48 ዓመታት መካከል ሊሆን ይገባል። በተጨማሪም የአካልም ሆነ የአዕምሮ ጉድለት የሌለበት፣ አስተዋይና በስነ-ምግባር የተመሰገነ ሰው መሆን አለበት።

ከያንዳንዱ ጎሳሉባሆኖ የተመረጠ ሰው ኦዳ ቡልቱም ከደረሰ በኋላአባ ጨፌለሚባለው ጊዜያዊ የሸንጎ አስተባባሪ ያመለክታል።አባ ጨፌ ወደርሱ የሚመጡትን ሉባዎች ተቀብሎ ወደተመደበላቸው የመኝታና የመመገቢያ ቦታዎች ይመራቸዋል። ጉባኤው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስም መስተንግዶውን በበላይነት ይመራል። ለጉባኤው የሚወጣውን ወጪ ሁሉ በበላይነት ይቆጣጠራል። የአባ ጨፌ ትልቁ ስራ ግን የኦዳ ቡልቱምንአባ ገዳማስመረጥ ነው። ይህንንም የሚያደርገው ጉባኤው በሚጀመርበት ዕለት ነው። ይህ የምርጫ ስነ-ስርዓት የሚፈጸመው ከየጎሳውሉባሆነው በጉባኤው የተገኙ ተሳታፊዎችጎሳችንን ይወክላልብለው በሚያቀርቧቸው እጩዎች መካከል በሚደረገው ፉክክር ነው። ጉባኤተኞቹ ከፍተኛ ድምጽ የሰጡት ሰውአባ ገዳሆኖ ይሰየማል።

አባ ገዳቃል በቃልየገዳው አባትማለት ነው። በአውዳዊ ፍቺውየዘመኑ አባትእንደማለት ሊሆን ይችላል። በእርግጥም ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ባሉት ስምንት ዓመታት (የአንድ ገዳ የስልጣን ዘመን) “አባ ገዳየህዝቡ አባት ተደርጎ ይቆጠራል። የመንግሥቱም ሆነ የጠቅላላው ሀገር ርዕሰ ብሔር በመሆን ያገለግላል። ህዝቡንም በልዩ ልዩ መድረኮች ላይ ይወክላል።

   ሌላው አባ ገዳትልቁ ስራጨፌ ገዳየተባለው ሸንጎ የሚያካሄደውን የስምንት ቀናት ጉባኤ መምራት ነው። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ይህ ጉባኤ በህብረተሰቡ ዘንድ እንደ ከፍተኛ የስልጣን አካል ይወሰዳል። በስምንቱ ዓመታት የተከናወኑ አበይት ድርጊቶች በዚህ ጉባኤ ይገመገማሉ። በዘመኑ ህዝቡን ሲያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎችም በታላቅ ስነ-ስርዓት ይሸኛሉ። ወደፊት የሚተገበሩ እቅዶችም ይወጠናሉ። ህብረተሰቡ የሚተዳደርባቸውናሴራተብለው የሚጠሩት ህጎችና ደንቦች ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ጉባኤው በሚያደርገው ውይይት እንዲሻሻሉ ይደረጋሉ። አስፈላጊ ሆነው የተገኙ ደንቦችና መመሪያዎችም እንደ አዲስ ይረቀቃሉ። በስተመጨረሻ ላይም ሸንጎው የወደፊቱን አስተዳዳሪዎች በመምረጥና የስልጣን ርክክብ በመፈጸም ጉባኤውን ያጠናቅቃል።

***********************************************************************
  * ጨፌ ገዳ''
ሸንጎ በሚያደርገው የአስተዳዳሪዎች ምርጫ የሚመረጡት ስድስት ሰዎች ናቸው። እነዚህም ሰዎች ለስምንት ዓመታት ሀገሩንና ህዝቡን የሚያስተዳድሩ ናቸው። በመሆኑም የምርጫው መስፈርት የሉባ (የሸንጎ አባል) ከሚመረጥበት መመዘኛ ስርዓት ጠበቅ ይላል። በዚህ መሰረትም ለመስተዳደሩ መሪነት የሚመረጠው ሰው በጀግንነቱ የተመሰገነ፣ የንግግር ችሎታ ያለው፣ የህዝቡን ባህልና ወግ በደንብ የሚያውቅ፣ የህግ እውቀቱ የተመሰከረለት፣ በስነ ምግባሩና በሐቀኝነቱ የተመሰገነ፣ በአካሉም ሆነ በአእምሮው ጤነኛ የሆነ ወዘተ.. መሆን ይገባዋል።

እነዚህ ስድስት እጩዎች የሚጠቆሙበት አሰራር ከትውፊት አዋቂዎች እንደሚነገረው በአንድ ወጥ ሁኔታ አይደለም። አንዳንዶችየየጎሳው ተወካዮች አንዳንድ እጩ ይጠቁማሉ:: ሌሎች ደግሞያለፈው ዘመን አስተዳዳሪዎች ተተኪዎቻቸውን ይጠቁማሉየሚል መረጃ ይሰጣሉ :: 


ይህ ወግኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲከተሰኘው የአፈንዲ ሙተቂ መፅሀፍ የተወሰደ ነው::

Comments

Popular posts from this blog

የደመወዝ ስኬል አፈጻጸም መመሪያ

በዜሮ ዓመት የወጣ ክፍት የስራ ማስታወቂያ

የነጥብ ስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት