የአለም ታላላቅ ሚዲያዎች አብይ ትኩረት
*ካይሮ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያቀረበችውን ንድፈ ሐሳብ አዲስ አበባ ውድቅ አደረገች*-አልጀዚራ
በዓባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው ትልቁ የኃይል ማመንጫ ግድብ ዙሪያ ያለውን ልዩነት ለመፍታት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ጥረት ያለውጤት መቋጨቱን ግብጽ አስታውቃለች፡፡
የግብጽ የመስኖ ሚኒስቴር ባለፈው ሰኞ ያወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ሱዳንን ጨምሮ ኢትዮጵያና ግብጽ የተሳፉበት የሁለት ቀናት ውይይት በአምስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እየተገነባ የሚገኘውን ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ቴክኒካዊ ጉዳይ ሳይዳስስ ተቋጭቷል፡፡
ግብጽ ግድቡ በውኃ ድርሻዋ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያመጣባት ሰግታለች፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ግድቡ በግብጽ የውኃ ድርሻ ላይ ተጽእኖ እንደሌለው በመግለጽ ግድቡ ግን ለምጣኔ ሀብታዊ ዕድገቷ አስፈላጊ መሆኑን ትናገራለች፡፡
የግብጽ ሚኒስትር እንዳሉት የኢትዮጵያ ልዑክ ከሰሞኑ ካይሮ ያቀረበችውን የውኃ አሞላልና የግድቡ አጠቃቀም ሁኔታ የመነሻ ሐሳብ አልተቀበለውም፡፡
በግብጽ የቀረበው የመነሻ ሐሳብ በዋነኛ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ አሠራር እንዲተገበር የሚጠይቅ ነው፤ በቀጣይ በሱዳን ካርቱም እንዲመከርበትም የሚያሳስብ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ ለሱዳንም ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በግብጽ ዲፕሎማቶች ዘንድ በተናጠል የተሰራጨው መረጃ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መሆኑን እንደሚያመለክት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰራጨውና ሮይተርስ ተመልክቸዋለሁ ያለው መረጃ አዲሱን የግብጽ ሐሳብ ‹‹በጥቅሉ ኢትዮጵያ ውድቅ አድርጋዋለች›› በማለት በኢትዮጵያ በኩል የቀረበውንም ሐሳብ ‹‹የተዛባና ፍትሐዊ ያልሆነ›› የሚል መሆኑን ዘግቧዋል፡፡
ማስታወሻው ቁልፍ ያላቸውን ልዩነቶች በዓመታዊ የወንዙ ፍሰት መጠንና በድርቅ ጊዜያት ስለሚኖረው የፍሰት ሁኔታ በማለት ነው የገለጻቸው፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው የሰኞው ውይይት ያለፍሬ መበተኑን እንደተናገሩም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረው በ2003 ዓ.ም ነበር፤ ከ6 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል እንደሚያመነጭ የሚጠበቀው ግድብ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ባለቤት ያደርጋታል፡፡
ባለፈው ጥር የኢትዮጵያ የውኃና ኢነርጅ ሚኒስትር እንደተናገሩት ግድቡ በቀጣዩ የአውሮፓውያኑ ዓመት መጨረሻ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል፤ በአውሮፓውያኑ 2020 ደግሞ ሙሉ በሙሉ ኃይል ያመነጫል፡፡ ምንም እንኳ በሁለቱ ሀገራት መካከል የቃላት ጦርነቶች ሲሰሙ የኖሩ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መለሳለስ ታይቶ ነበር፤ ነገር ግን ልዩነቶች ሳይዘጉ ቆይተዋል፡፡
ሮይተርስ አየሁት ባለው መረጃ ግብጽ ያቀረበችው አዲስ ሐሳብ በውኃ ሙሊቱና በግድቡ አጠቃቀም ዙሪያ ከሱዳንና ኢትዮጵያ ጋር አዲስ ስምምነት እንዲደረስ የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ እንዲወያዩም የሱዳንና ኢትዮጵያ የውኃ ሚኒስትሮችን ጠርተው ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጋዋለች፡፡ በምትኩም በ2018 (እ.አ.አ) ኢትዮጵያ አቅርባው በነበረው መነሻ ሐሳብ ላይ እንዲመክሩ ለሚንስተሮቹ ጥሪ አቅርባለች፡፡
በኢትዮጵያም በግብጽም የቀረቡት የውኃ አሞላል ምክረ ሐሳቦች አምስት ደረጃዎችን የያዙ ሲሆኑ የመጀመሪያው ደረጃ ሁለት ዓመታትን ፈጅቶ 595 ሜትር ድረስ እንዲሞላ ሀገራቱ ተስማምተዋል፡፡ በዚህም የግድቡ የኃይል ማመንጫ ሁሉም ተርባይኖች ሥራ መጀመር የሚችሉ ይሆናል፡፡
ነገር ግን ግብጽ ያቀረበችው አዲስ ሐሳብ ‹‹በ1979 እና 1980 (እ.አ.አ) ያጋጠመውን መሰል ድርቅ ቢከሰት ግድቡን ለመሙላት የታቀደው የሁለት ዓመት ጊዜ የግብጽን የአስዋን ግድብ ከፍታ ከ165 ሜትር በታች እንዳይወርድ በሚያደርግ አግባብ ሊራዘም ይገባል›› የሚል ነው፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ መስማማት የማይቻል ከሆነ ግብጽ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ የሥራ ዕድል ልታጣ እንደምትችልና 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከዓመታዊ ምርቷ ልታጣ እንደምትችል ስጋቷን ትገልጻለች፡፡ 300 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ልታጣ እንደምትችልም ሰግታለች፡፡
የመጀመሪ ደረጃው የግድቡ ሙሊት ከተጠናቀቀ በኋላም ግብጽ በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ በቋሚነት እንዲለቀቅ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ትፈልጋለች፤ የኢትዮጵያ ፍላጎት ግን እስከ 35 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ በዓመት መልቀቅ እንደሆነ ነው ግብጽ ያስታወቀችው፡፡
በመረጃው ላይ ባለፈው ወር ኢትዮጵያ የግብጽን መነሻ ሐሳብ ‹‹ግድቡን ለመሙላት የማያስችል ሁኔታ ነው›› በሚል ውድቅ እንዳደረገችው ተመላክቷል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ዕቅድ ለራሷ ያደላና የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳ ነው›› በሚል መረጃው በግብጽ እየተሠራጨ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
የዓባይ (ናይል) ወንዝን አጠቃቀም በተመለከተ በ1929 እና 1959 (እ.አ.አ) በእንግሊዝ አደራዳሪነት ግብጽና ሱዳን የዓባይ ወንዝን ለመከፋፈል ስምምነት አድርገው ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ግብጽ በዓባይ ወንዝ የላይኛው የተፋሰስ ሀገራት ግድብ እንዳይሠራ የመቆጣጠር ስልጣን በስምምነቱ አግኝታ ነበር፡፡ በዚህ ስምምነት የወንዙ ዋነኛ የውኃ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ አልተሳተፈችም፤ የውኃ ድርሻም አልተተወላትም፡፡ በተለይ በ1959 የተደረገው ስምምነት የናይልን ውኃ 66 ከመቶ ለግብጽ፣ 22 ከመቶ ለሱዳን እና ቀሪውን 12 በመቶ ደግሞ በትነት ምክንያት የሚባክን አድርጎ በማከፋፈል ኢትዮጵያንና ሌሎቹን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ባዶ ያስቀራል፡፡
በ2010 (እ.አ.አ) የናይል ተፋሰስ የላይኞቹ ሀገራት ከውኃው የተሻለ ተጠቃሚ የሚደርጋቸውን አዲስ የስምምነት ማዕቀፍ አቀረቡ፡፡ ግብጽና ሱዳን ግን የብቻ ተጠቃሚነታቸውን ለማስቀጠል ማዕቀፉን አልተቀበሉትም ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳና ኬንያ እየመሩት የስምምነት ማዕቀፉ ወደፊት ተራምዷል፤ በሂደትም ሱዳን ወደ ስምምነቱ ገብታለች፡፡
በዚህ ሂደት ላይ እያለ ነበር ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የጀመረችው፡፡ በ2015 (እ.አ.አ) ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በፕሮጀክቱ ዙሪያ የውይይት ማዕቀፍ አዘጋጁ፤ የመግባቢያ መርሆዎችንም አስቀመጡ፡፡ አንዳቸው የሌላኛውን ጥቅም ላለመጉዳትም መግባባት ላይ ደረሱ፡፡ በቅርቡ ግን ግብጽ ከዚህ ማዕቀፍ ውጭ የሆነ ሐሳብ ይዛ በመምጣት እንደገና ሽኩቻው እንዲያገረሽ አደረገች፡፡
Comments
Post a Comment