እንቁጣጣሽ- የአዲስ ዓመት ወግ

ዕንቁጣጣሽ-- የአዲስ ዓመት ወግ
***************************************

እንኳን ለአዲሱ አመት በሰላም አደረሳችሁ እያልን በበዓሉ ዋዜማ የእንቁጣጣሽ ወግ ይዘንላችሁ ቀርበናል:: ሐገራችን ኢትዮጵያ በታሪክ ቀደምትነት የስልጣኔ መገለጫዎቿ መካከል የዘመን አቆጣጠር ቀመሯ አንዱ ነው:: በዓለም 13 ወራቶች ያሏት ብቸኛዋ ሀገር ነች ኢትዮጵያ::

ዘመናት ዘመናትን እየወለዱ፣ ሰዓታት ደቂቃን ቅጽበትን /ሰኮንድን/ ሳይቀር እየሰፈሩ/እየቆጠሩ/ ዕለታት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን አሁን ላለንበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ዓውደ ዓመት ግእዝ ሲሆን አማርኛ የዘመን መለወጫ/ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕንቁጣጣሽ እየተባለም ይጠራል፡፡

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ወራት እንደ ቅብጢ (ግብፅ) ዘመን አቆጣጠር በመሰከረም 1 ቀን ይጀምራሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት የሮሜ መንግሥት ቄሣር አውግስጦስ 33 ዓመተ ዓለም ግብጽ ዓመት በዚያ ቀን እንዲጀመር ስለ ደነገገ ነው።

መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ /መስከረም/ ሲያትት «ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው እርሱም ግብጽ የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው በማለት ያስረዳል፡፡ የዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱ እኩል ፲፪ ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ቀኑ እየጎደለ ይሔዳል፡፡

ዘመን መለወጫ ለምን እንደተባለና ለምን መስከረም ወር ላይ እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዲህ በማለት ያትታሉ፡፡ ሲያትቱም ብርሃናት/ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን ጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱም ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ ዓመቱንም ጠንቀቀው ቢቆጥሩት ፫፻፷፬ (364) ቀናት ይሆናል፡፡ ለዘመን መታወቂያ ይሆን ዘንድ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብትን ፈጠረ ይላልና /መጽሐፈ ሔኖክ ምዕራፍ ፳፩ ቁጥር ፵፱፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ ዓለምን ውኃ አጥለቅልቋት ከቆየ በኋላ ዳግመኛ ከነበረው ውኃ የተገለጠችበት ወር «በመጀመሪያም ወር በምድር ታየች የንፍር ውኃው ከምድር ደረቀ» የሚለውን መሠረት አድረገው አቡሻኽር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስረዳሉ፡፡/መጽሐፈ ኩፋሌ ምዕ ቁጥር /

በመሠረቱ ዘመን ተለወጠ ሲባል የሚለወጡት ወራቱ ብቻ አይደሉም፡፡ በወቅቱ የሚከሰቱት/የተከሰቱት/ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር /ገጠመኝ/ ሲሆን ወራቶቹ ግን ያው በየዓመቱ እየተፈራረቁ ይመጣሉ፡፡ ዘመን መለወጫ ላይ የሰው ልጆች ሕይወት ሊለወጥ ይገባል፡፡ ተማሪው ተምሮ ወደቀጣዩ ክፍል /ደረጃ/ የሚለወጥበት፣ ገበሬው ክረምት ወራት በሚገባ ተጠቅሞ የሚቀጥለውን በጋ ወራት የሚቀበልበት፣ ሠራተኛው የክረምቱን ዝናብ ታግሶ የፀሐይን ወራት የሚቀበልበት ሌላውም እንደዚያ ሆነው ወራቶቹ በዚያ ዘመን ያለው የተፈጥሮ ክስተቶች የሚለወጥበት ዘመን ተለወጠ እየተባለ ይነገራል፡፡

ዓመታት ተፈጽመው አዲስ ዓመት ስንጀምር ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዓውደ ዓመት፣ አዲስ ዓመት ዕንቁጣጣሽ እየተባለ ይጠራል፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚያስረዱት ዕንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜው አመጣጥ ወይም ጥንተ ታሪክ በመጀመሪያ ኖኅ ለሦስቱ ልጆቹ አህጉራትን በዕጣ ሲያካፍላቸው አፍሪቃ ካም ደረሰችው፡፡ በአፍሪቃ ምድርም ሲገባ በመጀመሪያ ያረፈው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሀገሪቱም በአደይ አበባ አሸብርቃ ነበር፡፡ ወሩ ወርኃ መስከረም በመሆኑ ደስ ብሎት «ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ» ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል፡፡

ሁለተኛው የሀገራችን ንግሥት ንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሰሎሞን ዜና ጥበብ እየሰማች ስታደንቅ ትኖር ነበር፡፡ በጆሮዋ የሰማችውን በዓይኗ ዓይታ ለመረዳት ስለፈለገች በግመሎች ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኝ ኢየሩሳሌም የማይገኝ ልዩ ልዩ ገጸ በረከት አስጭና ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፡፡ ከንጉሡ ሰሎሞንም ጋር ተገናኝታ የያዘችውን ገጸ በረከት ከሰጠችው በኋላ ብዙ ነገሮችን ጠየቀችው፡፡ እርሱም አንድ ነገር ላይ ሰውሮ ሁሉንም ገለጸላት፡፡ ቤተ መንግሥቱንም፣ በቤተ መንግሥቱ የሚገኙ እጅግ በጣም የከበሩ ዕቃዎችን ሁሉ አስጎበኛት፡፡ ሲያበቃ «ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ» ሲል እጅግ በጣም የከበረ ዕንቁ አበረከተላት/ሰጣት/፡፡ ወሩም ወረኃ መስከረም ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት እንቁጣጣሽ የሚለው መጥቷል፡፡ አሁን ከሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት ደርሶ በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ የሚከበረውም መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡ አንድም «ዕንቁ ዕፅ አወጣሸ» ብሎ የአበባውን መፈንዳትን ያስረዳናል፡፡

ኢትዮጵያ ሕዝብ በየዓመቱ በታላቅ ስሜት ከሚያከብራቸውና ከሚያዘክራቸው በዓላት አንዱና ተወዳጅ የዘመን መለወጫ በዓል ነው። እንደ ዕፅዋት ሁሉ ሰው በመስከረም ላይ በተስፋ ስሜት ይለመልማል። ከቅዱስ ዮሐንስ ዋዜማ ጀምሮ በየቤቱ ጨፌ ቄጠማ ይጐዘጐዛል። አበባ በሥርዓት እየተዘጋጀ በየቦታው ይቀመጣል። በተለይም ልጆች አዳዲስ ልብሳቸውን ለብሰው በደስታ ይፈነድቃሉ። በአመሻሽ ላይ ችቦ አቀጣጥለው "እዮሐ አበባዬ መስከረም ጠባዬ፣ እዮሐ የበርበሬ ውኃ፣ በሸዋ በጐንደር በትግራይ በሐረር... ያላችሁ እንዴት ከረማችሁ፣ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ። እንጉርጉሮ ገባሽ በያመቱ ያምጣሽ.." እያሉ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች (በተለይ በገጠር) ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ ያድራሉ።

የሚያበሩት ችቦና የሚያነዱት እሳት በግርማ ምሽት ሲንቀለቀል ውጋገኑ ካገር አገር ከሰፈር ሰፈር ከቦታ ቦታ... ይታያል። በዕንቁጣጣሽ መዓልት በተደመረው አድባር ሰፈርተኞች ከርቀትም ከቅርበትም ይሰበሰባሉ። አባቶች ይመርቃሉ። "ዝናሙን ዝናመ ምሕረት፣ እህሉን እህለ በረከት ያድርግልን፣ ሰላም ይስጠን፣ እህል ይታፈስ፣ ገበሬ ይረስ፣ አራሽ ገበሬውን፣ ሳቢ በሬውን ይባርክ፣ ቁንጫን፣ አንበጣን፣ ትልን... ያጥፋ፣ ምቀኛን ሸረኛን ያጥፋ፣ ወጡ ገቡ ሰቡ ረቡ የሚለውን ሁሉ እግሩን ቄጠማ ዓይኑን ጨለማ ያድርገው፣ ያርገው፣ ያረገው፣..." ይባባላሉ።

እናት አባት ዘመድ አዝማድ በልጆቻቸውና በወዳጅ ዘመዶቻቸው የተበረከተላቸውን የዕንግጫ ጉንጉን (የአበባ አክሊል) በራሳቸው፣ እንጀራ ማቡኪያቸው፣ በመሶባቸው፣ በወጋግራቸው... ላይ ያስራሉ። ይህም የአበባ ጉንጉን ተፈትቶና ወጥቶ የሚቃጠለው መስቀል ደመራ ዕለት እሳቱ (አመዱ) ላይ በመጣል ነው። ተምሳሌቱም መጥፎ ውቃቢ እንዲቃጠልና በረከትም እንዲቀርብ ታስቦ ነው። ከምሽት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ በየቤቱ የተዘጋጀው ድግስ ይበላል፣ ይጠጣል።

በነጋታው የዕንቁጣጣሽ ዕለት ልጃገረዶች በሙሬ ወገባቸውን አስረው የሀገር ባህል ወይም ዘመናዊ ቀሚስ (ልብስ) ለብሰው አሽንክታብ ጨረቃ ጠልሰም፣ ብር ማርዳ (ዶቃ) ድሪ፣ መስቀል፣ የአበባ ጉንጉን በአንገታቸው ላይ አጥልቀው ዓይናቸውን ተኳኩለው፣ ፀጉራቸውን ጋሜ ቅርፅ ተሰርተው፣ ራሳቸውን አደስ አሪቲ የተቀመመ ለጋ ቅቤ ተቀብተው በራስ ማሰሪያ ሸብ አድርገው፣ የብር መስቀላቸው ላይ አሪቲ (ሪያ) ሰክተው፣ እጅና እግራቸውን እንሶስላ ሞቀው በክንዳቸው አምባር አስረው፣ ብርአልቦ በእግራቸው፣ ብር ቀለበት በጣታቸው አድርገው፣ ሎሚ በጉንፋቸው ይዘው አሥር አሥር በመሆን ክብ ይሰሩና በእጆቻቸው ጭንና ጭናቸውን መሬቱን እየተመተሙ ተንበርክከውና ቁጢጥ ብለው ድሪያ ይጫወታሉ።

በዕንቁጣጣሽ ዕለት ልጃገረዶች ከከንፈር ወዳጆቻቸው ጐን ለጐን በመሆን አራት የጨዋታ ዓይነቶችን በጭፈራ ያሰማሉ። በመጀመሪያ አሥር አሥር ይሆኑና በአራት ክብ ተከፋፍለው አርባ ልጃገረዶች ተንበርክከው መሬቱን እየተመተሙ "ዛጐሌ" የተሰኘውን ጨዋታ ያሰማሉ። "ዛጐሌ ጌታው ሎሌ አንደኛ ማር ይተኛ በሰውየው መንገድ ሰውየው ዘለቀ እይኔ እንደበረዶ ውኃ ሆኖ አለቀ። ቶፋ ቶፋዬ ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው ዛሬስ አመዶ ሊማታ ነው" ሲል ወንዶች ደግሞ ለዕንቁጣጣሽ የተገዛላቸውን እጀ ጠባብ፣ ኮት፣ ተፈሪ ሱሪ ባት ተሁለት... ለብሰው፣ ቀጭን ኩታ ደርበው፣ አሞግረው የያዙትን ዱላ አስቀምጠው የራሳቸውን ክብ ሰረተው ወደ ልጃገረዶቹ በመጠጋት የወንዶቹ አቀንቃኝ የሚያፈቅራትን ልጃገረድ በዓይኑ እየቃኘ፣የሚከተለውን ይላል-

"እዩት እዚያ ላይ ግራሩ መንታ፣ 
ዓይንሽ ያበራል እንደሎሚታ 
ተሎሚታውም ያንቺ ዓይን ይበልጣል 
እንደመስታወት ያንጠባርቃል። 
ዐደይ ዐበባ የመስከረሙ 
እነጉብሌ ወዴት ከረሙ 
ዐደይ አበባ የሶሪ ላባ 
እፍ እፍ በይን እንደ ገለባ..." እያለ ያሞግሳታል።

የተወደደችዋ ልጃገረድም ከወጣቱ ላይ የእርሷም ቀልብ ያረፈበት መሆኑን ካረጋገጠች በሗላ በተራዋ፣ 
እዩት እዚያ ላይ ከግራሩ ሥር 
ድስት ተጥዷል ቋንጣና ምስር 
ቋንጣው ይቅርና ይምጣ ምስሩ 
አንተን አሰኘኝ የፍቅሬ ዛሩ። 
ዐደይ ፈነዳ መስከረም ነጋ፣ 
እንግዲህ ልቤ ባንተ ላይ ይርጋ" ትለዋለች።

ልጃገረዶቹ እንደመሸሽ፣ ወንዶቹ ደግሞ እንደመከተል እያሉ ይቀራረባሉ። ልጃገረዶች የወንዶችን መጠጋት ሲያዩ፣ "ኖሩ፣ ኖሩ፣" ይላሉ። ወንዶቹም "ከበሩ ከበሩ" ብለው ይመልሳሉ። ከዚያም አንዷ ወጣት ወደምትፈልገው ጐረምሳ ዓይኗን እየወረወረች፣ "ጠላ ጠጣ የኔ ቀበጥባጣ..." ትላለች። የተወደደውም "ጠጥቻለሁ፣ ላይሽ መጥቻለሁ" ብሎ ይመልሳል። "ብታየኝ አንደዜ ሳመኝ፣" ብላ ታስቅበታለች። "ብስምሽ ይቆጣል ባልሽ" ብሎ በተራው ያስቃቸዋል። ወጣቷም "ባሉ ባሉ እርሱ የት አይቶ፣ ሲቆፍር ተደፍቶ" ትላለች። "ሲቆፍር ምቺው በድግር፣" ይላታል። "ድግር መና ያፋታልና ገና፣" ትላለች። 
ቢያፋታሽ፣ እኔ አለሁልሽ፣ 
ውሽማ ይብላ እንጂ በቅቤ ጠለላ 
ባልማ ምን ይላል ደረቁን ቢበላ፣ 
ያንቺማ ወዳጅ የኮራሽበት 
ከዳገት ቀረ እንደ በሬ እበት" ይላታል ሊሰማት የፈለገው ልጅ። 

ያገቡ ባልና ሚስቶች ዓይነት ጨዋታ ሲጨዋወቱ ይቆዩና ሁሉም ጐረምሳ የፈለጋትን ልጅ አባርሮ ይይዝና በነጠላው አከናንቦ ይሰማታል። ተሳሚዋ በቃ እስክታገባ ድረስ የከንፈር ወዳጁ ሆነች ማለት ነው። ልጃገረዶቹ አንሳምም ብለው ስለሚግደረደሩ በስንት ትግልና ጉልበት ነው የሚሳሙት። የሳመ ወጣት ሎሚ፣ ድሪ፣ አልቦ፣ ብር፣ ማርዳ... ይሰጣል። እነዚህን ጌጣጌጦች አስቀድሞ ነው የሚያዘጋጀው። የዕንቁጣጣሽ ዕለት ልጃገረድ ደፍሮ ያልሳመ ወጣት በፈሪነቱ ሲሳቅበት ይከርማል።

ከዚያ "ፍየሌን ነብር በላት" የተባለው ሁለተኛው የጨዋታ ዓይነት ይቀጥላል። የሳመው ወጣት እንደነብር ተመስሎ ይደበቃል። የሳማት ወይም ሊስማት የከጀላት ልጃገረድ ደግሞ በፍየል ግልገል እንድትመስል ትደረግና ተሸፋፍና ትቀመጣለች። ከዚያም ነብሩ እያጉረመረመ ይመጣል። ከዚያ ተው አያ ነብሮ ግልገሌን አትውሰዳት፣ አትውሰዳት፣ እያሉ ሴቶቹም ይጮሁበታል። እርሱ ግን እምቢ አሻፈረኝ ብሎ ከግልገሏ ላይ ዘልሎ ይከመርባታል። ይስማታል። ልጆቹ ዋይ ዋይ እያሉ የጩኸት ድምፅ ያሰሙና እያጨበጨቡና እየጨፈሩ፣ "ፍየሌን ነብር በላት ለቅዱስ ዮሐንስ አረዳት ለገና ብዬ ስደለድላት እንግጫዬ ደነፋ ጋሻውን ደፋ እንግጫዬ ሰሌን ልደቁሰው ኩሌን እንግጫዬ የወሩ ዘረዘረ ዳርዳሩ እንጉብሌ ሊሄዱ ናቸው ተጫነላቸው ፈረስ በቅሏቸው፣ ያው አማረበት ዓይነርግባቸው።"

በዕለተ ዕንቁጣጣሽ በተለይ የልጃገረዶች ጭፈራና ጨዋታ እየደራና እየሞቀ ይሄዳል። ተቀባዮቹ ያደይ እያሉ የሚከተለውን ይዘምራሉ። 
ዕንቁጣጣሽ ያደይ ዕንቁጣጣሽ
" በየት ገባና ቆነጠጠሽ" "
ቆነጠጠኝ ልቤን ልቤን ኩላሊቴን 
እናቴን ጥሩ መድኃኒቴን 
እሙ ካልመጣች መቸም አልድን 
እርሷን ካጣችሁ መቀነቷን 
አበባሽ አደይ አበባዬ..." 

ከዚያም ወንዶች "እንክሾ እንክሾ አባ ወልክሾ" የተሰኘውን ሶስተኛ ዘፈን እየጨፈሩ ወደልጃገረዶች ይጠጋሉ። በተለይ አንድ ወጣት ፍላጐት ያለው በአባ ጅቦ ተመስሎ እያነከሰ ወደልጃገረዶች መኸል ይገባና አውውው... ብሎ ይጮሀል። "ምነው አባ ጅቦ" ይሉታል ልጃገረዶቹ ከመኸላችሁ አንዷን ጥፍጥሬ (ወጣት ማለት ነው) ልጅ ትሰጡኝ ዘንድ ብዬ ነው" ይላል። "አባ ጅቦ ሐሙስ ተመለስ" ይሉታል ልጃገረዶች። ጅቡም ሐሙስ ሐሙስ ቶሎ ድረስ እያለና እያነከሰ ወደጫካው ይሄዳል። ከዚያ ይሰነባብትና (ቆይቶ) እንደገና አውውው... ብሎ እየጮኸ ሲመጣ የሚፈልጋትን ልጅ ጥለውለት ይሸሻሉ። ይሮጣሉ። ጅቡም ወጣቷን ተከታትሎ ይበላታል ማለት ነው፣ ይስማታል። 

የተበታተኑ ልጃገረዶች እንደገና ይሰበስቡና አራተኛውን የጨዋታ ዓይነት "ሸንበቆና ሸንበቆ" ይጫወታሉ። 
ሸንበቅና ሸንበቆ 
ሲወጣ አየሁ ተጣብቆ 
አትንጫጩ ልጆቼ 
እመጣለሁ ሰንብቼ 
ቋንጣ በለስ በልቼ 
ቋንጣ በለስ ይሉሻል ይኸውና ቅጠሉ 
ቀጥቅጭና ቅመሺው 
ወሮታውን ከቻልሺው 
ለዚህ ለዚህ ወሮታ 
አልጋ ሰርቶ መኝታ 
መሬት ወርዶ ጫጫታ 
አባ አበሻው ወንድሜ እኔ ውሃ ስቀዳ 
እርሱ ጥጃ ሲነዳ 
ገረፈችው በሳማ 
ያጤ ወንበር ሳይሰማ 
አጤ ወንበር ንጉሱ 
እያስቀዱ ሲቀምሱ 
እየዞሩ ሲገምሱ... ዛጐሌ ጌታው ሎሌ አነደኛ ማር ይተኛ..." ይላሉ።

በዚህ ሁኔታ ሲጨፍሩና ሲሳሳሙ ይውላሉ። የከንፈር ወዳጅ ያበጃሉ። በከተማው የእንቁጣጣሽ ባህል ደግሞ አበባዬ ሆይ ባልንጀሮቼ.. እያሉ ገንዘብ ይለምናሉ፣ ሲቀበሉም ከብረው ይቆዩን... ይላሉ። ገጠሬዎች ግን ይጫወታሉ እንጂ አይለምኑም።

መልካም አውደ ዓመት ይሁን!

Comments

Popular posts from this blog

የደመወዝ ስኬል አፈጻጸም መመሪያ

በዜሮ ዓመት የወጣ ክፍት የስራ ማስታወቂያ

የነጥብ ስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት