ብልፅግና ቅርብ ነው-ጀግና ለድህነት እጅ አይሰጥም


አንድ ሆነን ሀገራችን ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ከፍታ እናደርሳታለን!

ብልጽግና ቅርብ ነው
============
ሁለት የድህነት ዓይነቶች አሉ። የመጀመሪያው ቁሳዊ ፍላጎት አለመሟላት ነው። ለዚህ መነሻው ሁለተኛው የድህነት አይነት ሲከሰት ነው።


ሁለተኛው የድህነት አይነት የስነ-ልቦና ድክመት ነው። ነገን በጨለመ መነጽር መመልከት፤ ከልክ ያለፈ የይገባኛል ስሜት የስነልቦና ድህነት ተጠቂዎች የሚያሳዩዋቸው ዋነኛ ምልክቶች ሲሆኑ ከተስፋ ይልቅ ማማረርን ባህሪ አድርገው ይወስዱታል።

አብነት የሚሆን አንድ አጭር ታሪክ ልተርክ። አንድ ጫማን በመጥረግ የሚተዳደር ወጣት ደምበኛው ከሆነ የታክሲ ሹፌር ጋር እየተወያዩነው። ወጣቱ ከሊስትሮ የሚያገኘው ገቢ በቂ ስላለመሆኑ ይታወቃል ራሱ በካርቶን ባባጃጀው ሳጥን ሸቀጥ ጨምሮ መሸጥ ይፈልጋል። ቀስ ብሎም በመቆጠብ የራሱን ኪዮስክ መክፈት ያልማል። ሱፐርማርኬት፣ ሆቴል፣ ፋብሪካ ወዘተ ከህልሙ ሩቅ አለመሆናቸውን ያምናል። በዚህም ተስፋ ደስተኛ ሆኖ ከአላማው ሳይዘናጋ እየሰራ ይማራል፤ እየተማረ ይሰራል። በጨዋታቸው መሀል ለደምበኛው የቀን ገቢውን ይጠይቀዋል፣ የታክሲ ሹፌሩም በማማረር ምን ገቢ ትለዋለህ ተበልቶ፣ ተጠጥቶ፣ የቤት ኪራይ ተከፍሎ ቀሪውን ለመዝናኛ የማይበቃ ገቢ ትለዋለህ ጓደኞቼ ሚስት አግብተው ልጆች ወልደው ይኖራሉ እኔ ግን ይኸው የዕለቴን እየኖርኩኝ የማይቀየር ህይወይት እገፋለው። የተሳሳትኩት ይህንን ስራ ስራ ብዬ የያዝኩኝ ቀን ነው።

በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ግልፅ ነው፣ በገቢ ደረጃ የታክሲ ሹፌሩ ቢበልጥም ተስፋን በመሰነቅ ሊስትሮው በልጦታል። በሊስትሮነት እና በፋብሪካ ባለቤትነት መካከል ያለው ግምብ ጊዜ ብቻ ነው። በጥረት፣ በፅናት፣ በትዕግስት፣ በቁጠባ፣ አላማን ባለመሳት ያለጥርጥር ያሰበው ግብ ላይ ይደርሳል። ከቁሳዊ ድህነት ሙሉ በሙሉ የነጻ ማህበረሰብ፣ ግለሰብ፣ ሀገር እስካሁን የለም። ደረጃው ይለያያል እንጂ ሁላችንም ቢያንስ አንድ ቁሳዊ ችግር አለብን። ጤና ሊሆን ይችላል፣ መጠለያ ሊሆን ይችላል ወዘተ ነገር ግን ቁሳዊ ችግሮቻችንን አንድ በአንድ ለማሸነፍ ስነልቦናዊ ችግሮቻችንን ማከም ግድ ይለናል።

ከላይኛው ታሪክ የምንማረው ነገር ቢኖር ሀገር በተማረ ሀይል ብዛት፣ በመዓድን እና ነዳጅ ክምችት፣ በውጪ እርዳታና ኢንቨስትመንት ወዘተ ልትቀየር አትችልም። ሀገር የምትቀየረው በነዋሪዎቿ የስነልቦና ዝግጅት እና ጥንካሬ፣ ፅናትና አንድነት ነው።

የስነልቦና ድህነትን አፈር ድሜ አስግጠው ወደ ብልጽግና የሚንደረደሩትን በማበርታት፣ በዚሁ መስመር የበለጽጉትን አርአያነታቸውን በመከተል ተገቢውን ዕውቅና እና ክብር በመስጠት ተስፋ የቆረጡትን ስነልቦናቸውን በማከም፣ ድህነትን ታግለው ራሳቸውን እንዲያሸንፉት በማገዝ ወደ አሸናፊነት መስመር ማስገባት ያስፈልጋል።

ተስፋ የቆረጠ ዜጋ ሌብነትን ይለምዳል። ተስፋ የቆረጠ ማህበረሰብ ሀገርን ወደኋላ ይጎትታል።  የዛሬው ፈተናችን የኢኮኖሚ ኋላቀርነት ነው። የዛሬ ትውልድ ቀና ብሎ በኩራት ለልጆቹ የሚያወርሰው ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን ነው።

ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና እንደ አድዋ ጦርነት በአንድ ጀምበር ተጀምሮ የሚጠናቀቅ አይደለም። ፅናትን ይጠይቃል፣ ትዕግስትን ጥረትን ከእያንዳንዳችን ይፈልጋል። የዚህ ትውልድ ጀግንነት የሚለካው በስራ ብቻ ነው። መስዋዕታችን ላባችን ነው። ሀበሻ ምቀኛ ነው የሚለውን አሉታዊ ብሂል ሀበሻ ሲተባበር እንደ መንጠቆ ተያይዞ ነው የሚያድገው በሚል አወንታዊ ብሂል መቀየርን ይጠይቃል፣ በነገ ተስፋ ማድረግ አለብን። እየሰራን ተስፋ እናደርጋለን።

 ፈተናዎችን እየተቋቋምን ተስፋ እናደርጋለን። ምንም ይሁን ምን ተስፋችንን አንለቅም። ጀግና ተስፋ አይቆርጥም። የየራሳችንን የማደግ ዕድል በራሳችን እጅ ይገኛል። አገዙንም እናድጋለን፤ አላገዙንም እናድጋለ። ይህንን ካደረግን ብልጽግና ቅርብ ይሆናል። ለቅንጦት የማንሸነፍ ከሆነ ብልጽግና ቅርብ ነው። ቅንነት በልባችን ካሳደርን ሌላ የሚይዘን ምንም ምን ምክንያት አይኖርም፣ ብልጽግና በጣም ቅርብ ነው።

ጉዞ ወደ ብልጽግና ማማ!

Comments

Popular posts from this blog

የደመወዝ ስኬል አፈጻጸም መመሪያ

በዜሮ ዓመት የወጣ ክፍት የስራ ማስታወቂያ

የነጥብ ስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት