4ተኛው ዙር የህዝብ ቤት ቆጠራ::
1 የህዝብ ቤት ቆጠራ ትርጉም::
የህዝብ ቤት ቆጠራ በተወሰነ ወቅት እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ወይም በሀገር ውስጥ በተወሰነ የአስተዳደር ክልል ስለአለው የህዝብ ብዛት እና የስነ- ህዝብ ባህሪያት፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ወይም በተወሰነ የአስተዳደር ክልል ስለሚገኙ ቤቶች ብዛት ፣ስለ ቤቶች ሁኔታ የሚገልፁ ስታስቲካዊ ሁኔታ መረጃዎችን የመሰብሰብ ፣የማጠናቀር፣የመተንተን፣ትክክለኛነቱንም በመገምገም የትንተና ሪፖርት ማዘጋጀት እና የተገኘውን ውጤት ለተጠቃሚዎች የማሰራጨት ተግባራትን ያጠቃልላል፡፡ የህዝብ እና የቤት ቆጠራ ውጤት ከአነስተኛ የአስተዳደር ክልል ማለትም ከገጠር እና ከተማ ቀበሌ አስተዳደር እሰከ ብሄራዊ ክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ መረጃዎችን ያስገኛል፡፡
2 የአራተኛው ዙር ቤት ቆጠራ አስፈላጊነት
በሀገራችን እስካሁን ድረስ ሶስት ጊዜ አገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራዎች የተካሄዱ ሲሆን የመጀመሪያው 1976ዓ.ም እና ሁለተኛው በ1987ዓ.ም ሶስተኛው ደግሞ 1999ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ በነዚህ ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ የህዝብ ብዛት እና ስርጭት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ሁኔታ ለውጦች ተከስተዋል፡፡ ስለዚህ ከ1999 ዓ.ም የህዝብ እና ቤት ቆጠራ የተገኙትን መረጃዎች ወቅታዊ ለማድረግ፣የተከሰቱትን ለውጦች ለመገምገም ፣አዳዲስ መረጃዎችን በጥራት ለመሰብሰብ እንዲሁም የህዝቡን የወደፊት የስነ ባህሪያት ፣የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አስተማማኝ እና ወቅታዊ ከሆኑ መረጃዎች በመነሳት ለመተንበይ በመጋቢት 29/2011 ዓ.ም የሚካሄደው ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ አስፈላጊ ነው፡፡
3 የአራተኛው ዙር የህዝብ እና ቤት ቆጠራ ዓላማ
የህዝብ ቆጠራው ዋነኛ አላማ ለዕቅድ ዝግጅት፣፤ለፖሊሲ ቀረፃ፣ለአገልግሎት አሰጣጥና የስነ ህዝብ ፖሊሲ አፈፃጸምን ለመገምገም የሚያስችሉ ወቅታዊ እና አስተማማኝ የስነ ህዝብ ማህበራዊ መረጃዎችን በማግኘት የኢትዮጵያውያንን የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል ማድረግ
4 ከአራተኛው ዙር ህዝብ እና ቤት ቆጠራ የሚገኙ መረጃዎች ያላቸው ጠቀሜታ፡፡
- የትምህርት ዘርፉን ጥራት እና ተደራሽነት ለማሻሻል በየጊዜው ለሚዘጋጁ እቅዶች እና ፖሊሲዎች
- የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽ እና ጥራትን ለማሻሻል ለሚዘጋጁት እቅዶች እና ፖሊሲዎች፡፡
- ለዜጎች በቂ የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል እቅድ ለማዘጋጀት እና ተግባራዊነቱንም ለመከታተል እና ለመገምገም፡፡
- የሀገሪቱ ህዝብ ግማሽ ክፍል የሆኑትን ሴቶች በማህበራዊ፣በኢኮኖሚያዊ እና በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚዘጋጁ እቅዶች እና ፖሊሲዎች፡፡
- የተለያዩ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በተለይም የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ድርቅ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ በዘለቄታዊነት ለማቋቋም የሚያስችል እቅዶዶች እና ፖሊሲዎች ለማዘጋጀት
- የህዝብ እድገት ከተፈጥሮ ሀብት እና ከባቢ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ ለሚዘጋጁ እቅዶች እና ፖሊሲዎች፡፡
- የዜጎች የመሰረተ ልማት ፍላጎት(ንጹህ ውሃ፣መብራት፣ቴሌኮምኒኬሽን፣መንገድ ፣የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና ለመሳሰሉት)ተደራሽነትን እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ፡፡
- የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው እና በእድሜያቸው ምክንያት ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች በሀገሪቱ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ውስጥ እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለማድረግ ለሚቀረጹ ፖሊሲዎች ፡፡
- ለንግድ ኢንቨስትመንት እና ኢንደስትሪ ልማት አገልግሎትን ለማስፋፋት ለሚነደፉ አስትራቴጅዎች ለእነዚህ እና ለመሳሰሉት ከህዝብ እና ቤት ቆጠራ የሚገኙ መረጃዎች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡
5. የአራተኛ ዙር የሕዝብና ቤት ቆጠራ መቼና እንዴት ይካሄዳል?
• ቆጣሪዎች በተመደቡበት አካባቢ በተዘጋጀላቸው የቆጠራ ቦታ ካርታ እየታገዙ ከመጋቢት 27 – 29 ከቤት ወደ ቤት በመሄድ በመጀመሪያ በቆጠራ ቦታው ውስጥ የተካለሉ ቤቶችን፣ ቤተሰቦችንና ድርጅቶችን ይመዘግባሉ፡፡
• ቆጠራው በመላ ሀገሪቱ በገጠርና በከተማ በአንድ ተመሳሳይ ቀን መጋቢት 29/2011ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ለቆጠራው አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ምዝገባው በተከናወነበት ሁኔታ ከመጋቢት 29- ሚያዝያ 20፣ 2011ዓ.ም ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ዝርዝር መረጃ ይሰበሰባል፡፡
6. በአራተኛ ዙር የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚሰበሰቡ መረጃዎች ይዘትና ዝርዝር
ሀ. ሕዝብን በተመለከተ የሚሰበሰቡ መረጃዎች
• ጾታ፣ ዕድሜ፣ ሃይማኖት፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ የብሔር ብሔረሰብ
• የትምህርት፣ የአካል ጉዳተኝነት፣ የጋብቻና የሥራ ሁኔታዎች
• ሴት የቤተሰብ አባላት ሲሆኑ የወለዱ ከሆነ ስለልጆቻቸው ብዛት
• ወላጆቻቸውን ስላጡ ሕጻናትና ወጣቶች፣
• ስለፍልሰት፣
• በቤተሰቡ ውስጥ ስለተከሰተ ሞት የሚመለከቱ … ወዘተ መረጃዎች ይሰበሰባሉ፡፡
ለ. ቤቶችን በተመለከተ የሚሰበሰቡ መረጃዎች
• የቤቱ ዓይነት፣ የቤቱ ዕድሜ
• የቤቱ ግድግዳ፣ ጣሪያ፣ ኮርኒስና ወለል በአብዛኛው ከምን እንደተሠራ፣
• ቤቱ ያሉት ክፍሎች ብዛት፣
• ቤቱ ያለው የመጸዳጃና የማዕድ ቤት ዓይነት፣
• ቤተሰቡ በምን ዓይነት ማገዶና መብራት እንደሚጠቀም፣
• ቤተሰቡ የመጠጥ ውኃ ከየት እንደሚያገኝ፣
• በቤቱ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና መደበኛ ስልክ ስለመኖሩ ወዘተ መረጃዎች ይሰበሰባሉ፡፡
7. በቆጠራው የሚካተቱት እነማን ናቸው ?
• በመደበኛ ቤታቸው የሚኖሩ ሰዎች
• በሆቴል፣በሆስፒታል እና በሌሎች የጋር እዮሽ መኖሪያዎች ማለትም በአዳሪ ትምህርት ቤቶች፣ በህጻናት ማሳደጊያዎች፣ በሰራተኛ ካምፖች፣ በእስር ቤቶች፣ በገዳሞች ወዘተ የሚኖሩ ሰዎች፡፡
• መጠለያ ቤት የሌላቸው(የጎደና ተዳዳሪዎች፣ቤተክርስቲያን ፣ መስጊዶች፣ በመቃብር ቤቶች እና በመሳሰሉት ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች)
• በአጠቃላይ ጨቅላ ህጻናት፣ታመው አልጋ ላይ ያሉ ሰዎች፣አካል ጉዳተኞች፣ወጣት ወንዶች እና ሴቶች፣የውጭ ሀገር ዜጎች ሁሉም በቆጠራው ይካተታሉ፡፡
8 .በቆጠራው መተግበር ያለባቸው መርሆዎች
• ማንኛውም ሰው መቆጠር አለበት
• እያንዳንዱ ሰው መቆጠር ያለበት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡
9. በቆጠራው ወቅት ቆጣሪዎችን እና ተቆጣጣሪዎችን እንዴት እንለያቸው፡፡
ቆጣሪዎች ሆኑ ተቆጣጣሪዎች የቆጠራው ሰራተኞች ስለመሆናቸው የሚገልጽ የቆጠራ ባጅ እና ደብዳቤ ይኖራቸዋል፡፡በተጨማሪም ለስራው የሚለብሱት ኮፍያ እና የሚይዟቸው ቦርሳ እንዲሁም የቆጠራ መጠይቆች እና ቅጾች የቆጠራ ኮሚሽን አርማ ይኖራቸዋል፡፡ እነዚህን ማረጋገጫዎች ያልያዘ ቆጣሪ ወይም ተቆጣጣሪ የሚል ሰው የቆጠራው ሰራተና ባለመሆኑ ሁኔታውን ወዲያውኑ ጉዳዩ ለሚመለከተው ህጋዊ አካል ማሳወቅ ይገባል፡፡
10.ለቆጣሪው ስኬታማት ከህብረተሰቡ የሚጠበቅ ትብብር፡፡
• ቆጣሪዎች ወደየቤቱ በሚሄዱበት ጊዜ ቤት በመገኘት ለሚጠይቁት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን፡፡
• ለሚጠይቁት ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ ለአገር ግንባታ ለሚታቀዱ የልማት ዕቅዶችና ፖሊሲዎች መሰረታዊ ግብዓት የሆኑ መረጃዎችን የሚያስገኝ መሆኑን በመረዳት ትክክለኛ ምላሽ መስጠት፡፡
• በሚገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለቆጠራው ዓላማ እና ጠቀሜታ ለጎረቤቶቻችን በተለይ ላልተማሩ ወገኖች ቆጠራውን አስመልክቶ በተለያየ መንገድ የሚተላላፉ መልዕክቶችን ይዘት በማብራራት በቂ ግንዛቤ እንዲፈጥር በማድረግ ድርሻውን መወጣት አለብን፡፡
Comments
Post a Comment