የዓለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረት


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) መጋቢት 24 በትረ ስልጣናቸውን በህዝብ እንደራሴዎች ፊት ከተቀበሉ ወዲህ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረታቸውን በአዲሱ መሪ ላይ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ወቅቶች ባደረጓቸው ንግግሮች ውስጥ ያቀረቧቸው የወደፊት ዕቅዶች እና አቅጣጫዎች  እንዲሁም ተጨባጭ እርምጃዎች የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን  የማይጠበቅ ነገር ግን እየሆነ ያለ ታላቅ ለውጥ ሲሉ ዘግበውታል፡

የአሜሪካው የዜና አውታር ሲ ኤን ኤን ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባወጣው ዘገባ አብይ አህመድ ላለፉት ሁለት ወራት በሰሯቸው ተግባራት በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ ጀግና ተቆጥረዋል ሲል ያወሳል፡፡ የህዝብን ስሜት በመረዳት ሀገሪቱን ለማዘመን እየሰራ ያለ መሪ ነውም ብሏል፡፡
የሲ ኤን ኤን ዘገባ መነሻው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአሶሳ እስከ ጅጅጋ፣ ከመቀሌ እስከ ሀዋሳ  በሁሉም አቅጣጫዎች በመንቀሳቀስ ከህዝብ ጋር ያደረጉት ውይይት ነው፡፡ በእርግጥም በዚህ ውይይት የህዝብ ስሜት ተረድተዋል፣ ህዝቡም ለለውጥ እንዲዘጋጅ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ እናም የድረ-ገጹ ምልዕከታ ከዚህ የመነጨ ነው፡፡
የእንግሊዙ ደይሊ ሜል ድረ-ገፅ በበኩሉ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፍተኛ ለውጦችን እያደረገ ያለ መሪ ነው ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ለውጡን ማስቀጠሉ ላይ ግን የህዝቡ ድጋፍ ወሳኝነት ይኖረዋል ሲል አስቀምጧል፡፡
በተለያዩ ጉዳዮች ግንኙነቱ በሻከረ ህዝብ ውስጥ መሪ ሆኖ መገኘት ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሻለች ሀገር ለመገንባት አንድ ሆነን መስራት ተገቢ ነው እያሉ ያሉት፡፡ ይህ ሲሆን ስንወድቅም ስንነሳም በጋራ ይሆናል ያሉት፡፡እናም የደይሊ ሜይል ስጋት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት አድርገው እየሰሩበት ያለ ይመስላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገና በወራት የስልጣን ጊዜያቸው ህዝቡ ተስፋ እንዲኖረው የሚያደርግ ንግግር እና ለሙሰኞች ቀይ መስመር ማስቀመጣቸው  በድረ-ገጹ በጎ ጅምር ተብሏል፡፡
ይህንን ለማስረገጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ሁሉም የሚዘርፈው በቂ ሀብት እንደሌላት መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳድር እና የፍትህ ማጣት እንዲሁም የኑሮ ውድነት እና የስራ ማጣት ባለፉት ሶስት ዓመታት ህዝቡን ወደ አደባባይ ሲገፉ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም የዚህን ችግር መፍትሔ መስጠት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀዳሚ አጀንዳ መሆኑ የግድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ፋይናሽያል ታይምስ የአፍሪካ ወጣቱ መሪ በኢትዮጵያ ለዓመታት በዘለቀው ዘርፈ ብዙ ቀውስ ምክንያት መፈተኑ አይቀርም ሲል የዘገበው፡፡
በሀገሪቱ ለዓመታት እንደ ትልቅ ችግር የሚወሳውን ሙስና ለመዋጋት እና የህዝቡን መብት ለማረጋጥ የገቡት ቃል  መልካም ጅምር ነው ሲል ድረ ገፁ አሞግሷል፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፉት ሁለት ወራት ባቀረቧቸው ንግግሮች ውስጥ ተጨባጭ ማብራሪያዎችን ብቻ ሳይሆን አሳምሮ ማቅረብን የሚችሉ መሪ መሆናቸውን ብዙዎቹ ይስማሙበታል፡፡ ፋይናሽያል ታይምስ ድረ-ገፅም  የአብይ አህመድን ጠንካራ ንግግሮች ከአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጋር አመሳስሏቸዋል፡፡ ሁለቱም መሪዎች ጥሩ ተናጋሪ እና መፍትሔ ሰጪ ናቸው ሲል ያስቀምጣል፡፡
ይህ ድረ-ገፅ ስልጣናቸውን ሳያመነቱ የሚጠቀሙ እንደሆኑም አስፍሯል፡፡ ለምሳሌነትም በፍጥነት የአስችኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳታቸው፡ ቱባ ሹማምንቶችን ከቦታቸው ገለል ማድረጋቸው እና በሽብር፣ በመፈንቀለ መንግስት ሙከራ እንዲሁም በሙስና ክስ የተያዙ  እስረኞችን መልቀቃቸውን  በማስረጃነት ያቀርባል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያንም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ፡፡ እርሳቸው በትረ ስልጣኑን ከተረከቡ ወዲህ ብዙ ቤተሰቦች ከማረሚያ ቤት የናፈቋቸውን ዘመድ አዝማድ ተቀብለዋል፡፡በህዝብ ደንታ የሌላቸው እና ሙሰኞች ሲባሉ የከረሙ ሹማምንቶችንም ከስልጣናቸው ገለል አድርገዋል፡፡ ይህም በህዝቡ ዘንድ ተስፋ ሰጪ መሆኑ አልቀረም፡፡
ይሁን እንጂ ይላል ድረ-ገፁ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘርፈ ብዙ ችግር ባለባት ሀገር ውስጥ ቀጣይነት ያለው ተጨባጭ ለውጦችን ማቅረብ የማይችሉ ከሆነ የህዝቡ ተቃውሞ መቀጠሉ የማይቀር ነው ሲል ምልከታውን ያስቀምጣል፡፡
በትክክልም ይህ የብዙዎቹ ስጋት ነው፡፡ ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምረን እንስራ ውትወታ እና የተቋም ለውጥ ከአዲስ እይታ መርህ ጋር ተዳምሮ ለውጥ ለማስገኘት ሁነኛ መፍትሔ መሆኑ  እንደማይቀር የብዙዎቹ ግምት ነው፡፡
የአሜሪካው ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ በከፍተኛ አለመረጋጋት እና በብድር ዝቅጠት ውስጥ ለነበረችው ኢትዮጵያ መፍትሔ ሰጪ መሪ  ያገኘች ይመስላል ሲል አትቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የውጭ ዕዳ ሀገሪቷን የሚያንገዳግዱ ተግዳሮቶች መሆናቸውን በተደጋጋሚ እየገለፁ ነው፡፡ለዚህም መፍትሔ ይሆን ዘንድ በውጭ ሀገር ዶላር ያስቀመጡ ባሀብቶች እና ባለስልጣናት እንዲመልሱ የማግባባት ስራ በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አገራት ድጋፍ እንዲሰጡ ዲፕሎማሲያው ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በመንግስት ስር የሚገኙ ግዙፍ ተቋማትን ለግሉ ዘርፉ ለማካፈል ያስቀመጡት አቅጣጫም ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ነው፡፡ እናም ዋሽንግተን ፖስት በዘገባው ሀገሪቱ ለችግሯ መፍትሔ ሰጪ መሪ ያገኘች ይመስላል ሲል መነሻው እነዚህ ጅምሮች መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡
ብዙ አመራሮች ሙሰኛ እና ጥቅመኛ ተብለው በሚብጠለጠሉበት አገር ውስጥ መልካም አመራሮችን በአንድ ጀምበር ለይቶ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህም ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ ለዚህም ነው በህዝብ ዘንድ እንደ ትልቅ ሙሰኛ የሚጠቀሱ አመራሮች ቦታ ቀይረው ሲቀመጡ ለፖለቲካው ነው ወይስ መስረቃቸው ባለመረጋገጡ የሚል ጥያቄ እያስነሳ ያለው፡፡
ይህ ጉዳይ በአልጀዚራም ዘገባ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በካቢኒ ሹም ሽራቸው በህዝብ ዘንድ ችግር እንዳለባቸው የሚታሙ አመራሮችን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ መልሰው ማስቀመጣቸው አነጋጋሪ ሆኗል ሲል ያቀረበው፡፡
ይህ ስጋት እንደ እንዳንድ ዜጎች ከአልጀዚራ ጋር ይዝለቅ እንጂ አልጀዚራ ቀጥሎም  ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሯቸው ስራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው በማለት አስቀምጧል፡፡
ዘ-ኢኮኖሚስት ድረ -ገፅ እንዳሰፈረው ደግሞ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስገራሚ አጀማመር እያሳየ ነው ሲል ዘገባውን ጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላም ለማስፈን እና የግሉን ዘርፍ ለማነቃቃት የያዙት ውጥን ፍሬአማ እንደሚሆን አመላካች መንገድ ተከትለዋል ሲልም አስቀምጧል፡፡
ባለፈው ወር ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ውስጥ ያለውን ተቀባይነት የሚያሳይ አንድ ጥናት ይፋ ሲደረግ 84 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በአብይ አህመድ አመራር ደስተኛ መሆናቸው መገለፁ የሚታወስ ነው፡፡
                                          source : EBC

Comments

Popular posts from this blog

የነጥብ ስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት

አዋጅ ቁጥር 1064/2010

የደመወዝ ስኬል አፈጻጸም መመሪያ