የዓለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረት
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) መጋቢት 24 በትረ ስልጣናቸውን በህዝብ እንደራሴዎች ፊት ከተቀበሉ ወዲህ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረታቸውን በአዲሱ መሪ ላይ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ወቅቶች ባደረጓቸው ንግግሮች ውስጥ ያቀረቧቸው የወደፊት ዕቅዶች እና አቅጣጫዎች እንዲሁም ተጨባጭ እርምጃዎች የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የማይጠበቅ ነገር ግን እየሆነ ያለ ታላቅ ለውጥ ሲሉ ዘግበውታል፡ የአሜሪካው የዜና አውታር ሲ ኤን ኤን ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባወጣው ዘገባ አብይ አህመድ ላለፉት ሁለት ወራት በሰሯቸው ተግባራት በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ ጀግና ተቆጥረዋል ሲል ያወሳል፡፡ የህዝብን ስሜት በመረዳት ሀገሪቱን ለማዘመን እየሰራ ያለ መሪ ነውም ብሏል፡፡ የሲ ኤን ኤን ዘገባ መነሻው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአሶሳ እስከ ጅጅጋ፣ ከመቀሌ እስከ ሀዋሳ በሁሉም አቅጣጫዎች በመንቀሳቀስ ከህዝብ ጋር ያደረጉት ውይይት ነው፡፡ በእርግጥም በዚህ ውይይት የህዝብ ስሜት ተረድተዋል፣ ህዝቡም ለለውጥ እንዲዘጋጅ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ እናም የድረ-ገጹ ምልዕከታ ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ የእንግሊዙ ደይሊ ሜል ድረ-ገፅ በበኩሉ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፍተኛ ለውጦችን እያደረገ ያለ መሪ ነው ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ለውጡን ማስቀጠሉ ላይ ግን የህዝቡ ድጋፍ ወሳኝነት ይኖረዋል ሲል አስቀምጧል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ግንኙነቱ በሻከረ ህዝብ ውስጥ መሪ ሆኖ መገኘት ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሻለች ሀገር ለመገንባት አንድ ሆነን መስራት ተገቢ ነው እያሉ ያሉት፡፡ ይህ ሲሆን ስንወድቅም ስንነሳም በጋራ ይሆናል ያሉት፡፡እናም የደይሊ ሜይል ስጋት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት አድር...